ሩስያ በዲጂታላይዜሽን፣ በመረጃ መረብ ደህንነትና በዲጂታል ክህሎት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግ ገለጸች

173

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 ሩስያ በዲጂታላይዜሽን፣ በመረጃ መረብ ደህንነትና በዲጂታል ክህሎት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግ አስታወቀች።

የኢኖቬሽንንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ ኤች ዲ) ከሩስያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺንና ከልዑካቸው ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ሩሲያ መደገፏን አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

በተለይም በዲጂታል ክህሎት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ ሩስያ ያላትን የዳበረ ልምድ ኢትዮጵያ መካፈል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

የሩስያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ ምክትል ሚኒስትር ማክሲም ፓርሺን ሩስያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በኤሌክትሮኒክ የመንግስት አገልግሎት፣ በዲጂታል ክህሎት፣ በመረጃ መረብ ደህንነት እና በሌሎችም ዘርፎች በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ሩስያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ የትብብር ዘርፎች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም