ኤች አይ ቪ ኤድስ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 ኤች አይ ቪ/ኤድስ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በዚህም በኢትዮጵያ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን የምክርና ምርመራ አገልግሎት በስፋት መከናወኑ የሚቀጥል መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።

የዓለም የኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ስለበሽታው አጠቃላይ ሁኔታና እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ የጤና ችግር በማስመልከት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኤች አይ ቪ/ኤድስ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የምርመራና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

በደማቸው ቫይረሱ ያለባቸው ታማሚዎችም ራሳቸውን አውቀው ሕክምና እንዲጀምሩ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰው መድኃኒቱን እንዲጠቀሙ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ከፍ ያለ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

የእለቱን መከበር ምክንያት በማድረግ የቅድመ-መከላከል ሥራን ከማጠናከር ባለፈ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የምርመራና ምክር አገልግሎት በስፋት ይሰጣል ነው ያሉት።

እ.ኤ.አ. በ2030 ኤች አይ ቪ/ኤድስ አገር አቀፍ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ይሰራልም ብለዋል፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም