በድርቅና ሌሎች ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

125

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 በድርቅና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሲሆን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራሁ ተክለማሪያም፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተገኝተዋል።  

ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የሚተገበር መሆኑም ተጠቅሷል።          

ፕሮጀክቱ በድርቅ፣ ጎርፍና በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በሚቆይባቸው ጊዜያት 54 ሺህ 400 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከ18 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተመድቦለታል።

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ወጪ የተገኘው ከስዊዲን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብርና ከሲዊዘርላንድ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጄንሲ መሆኑም ተጠቁሟል።   

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራሁ ተክለማሪያም፤ በኢትዮጵያ በግጭት፣ በድርቅና በተፈጥሮ አደጋዎች ቀላል የማይባሉ ዜጎች ችግር ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይም አደጋዎቹን ተከትሎ የሚከሰተው የአገር ውስጥ ፍልሰት ለልማት ትልቅ ፈተና በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተለይም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ጥረቱን ስለሚያግዝ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።         

በሁለቱ ክልሎች የሚተገበረው ፕሮጀክት በሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እንደ መማሪያ ይሆናል ሲሉም አብራርተዋል።  

በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መስራት የሀብትና ጊዜ ብክነትን ለመቆጠብ እንደሚረዳ ጠቁመው በዚህ ረገድ መሰል ፕሮጀክቶች አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ድጋፍ ላደረጉ የልማት አጋሮችም አመስግነዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፤ በሱማሌና አፋር ክልሎች በአደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ድርጅቱ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅትና ዩ ኤን ሀቢታት ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

በተለይም በአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ከክልሎችና ከአካባቢዎቹ አስተዳደር ጋር በትብብር እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።     

ከሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ባሻገር በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአንበጣ መንጋ፣ በድርቅና ጎርፍ አደጋ ለችግር የተጋለጡ በርካታ ዜጎች የእኛን ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።  

በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ሃንስ ሄኔሪክ ሉንድኪውስት፤ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም