በአረንጓዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

315

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 በአረንጓዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ሲግናል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ እናት በመኖሪያ ግቢያቸው በአትክልት ልማትና በእንስሳት እርባታ እያከናወኑት ያለውን ሥራ ጎብኝተዋል።

በመዲናዋ ለረዥም ዓመታት የኖሩት ወይዘሮ አበራሽ ዋቅጅራ፤ በመኖሪያ ግቢያቸው አትክልት፣ የዶሮና ከብት እርባታ፣ የንብ ማነብና ሌሎችም ሥራዎችን ማከናወን ከጀመሩ ከአምስት ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል።

የእኚህን ጠንካራ እናት የከተማ ግብርና ሥራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥፍራው ተገኝተው የጎበኙ ሲሆን ተግባራቸው ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል እንደ አገር ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ ልማት የተከናወኑ የልማት ሥራዎችንና በቅርቡ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት ጠቅሰዋል።

በመኖሪያ ግቢያቸው ከጓሮ አትክልት ልማት ባለፈ በእንስሳት እርባታ የወተት፣ እንቁላልና ማር ምርቶች እያከናወኑ ያሉት እናት ለበርካቶች አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የራስን ምግብ የማምረት ሥራዎች ባህል ሆነው ከቀጠሉ በቤተሰብ፣ በአካባቢ አልፎም በአገር ደረጃ የምግብ ፍጆታን ለማሟላት ይጠቅማል ነው ያሉት።

በርካታ ፍላጎቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ በምግብ ራሳችንን ካልቻልን ተጎጂዎች እንሆናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት አለብን ብለዋል።

የአትክልት ልማትና የእንስሳት እርባታ ከበፊት ጀምሮ የሚወዱት ሥራ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ አበራሽ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ጉብኝት አስደምሞኛል ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ከግቢያቸው አልፎ በሰፊ መሬት ላይ ጭምር የማልማት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመኖሪያ አካባቢያችን በሚኖሩ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ማልማት ከቻልን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መጥቀም እንችላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት፣ በስንዴ፣ ሩዝና ሌሎችም የግብርና ምርቶች ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም