የሰላም ስምምነቱ በቀጣናው ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

181

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊ ክብር ሙሉ በሙሉ ባከበረ መልኩ እንዲፈታ ስምምነት መደረሱ በቀጠናው ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ አካሄድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 48ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢጋድ አባል አገራት የሰጡት ያልተቋረጠ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ምስጋና የሚያሰጠው ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩ ሲሆን በአየር ንብረት ለውጥ እና እያደረሰ ባለው ተፅዕኖ ዙሪያም ያላቸውን ስጋት የገለፁ ሲሆን ይህን ለመግታትም አባል ሀገራት እና አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ኢጋድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን በቅርብ በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዋና ፀሀፊው ኢጋድ ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን፣ ድርቅን፣ ተባይ እና ወቅታዊ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ምላሽ ለመስጠት ከአባል ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።.

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት፣ የሰብዓዊነት ሪፖርት የሚያዳምጥ ሲሆን በዛሬው እለትም ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም