ለደሴ ሆስፒታል መቋቋሚያ የሚውል የ80 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

364

ደሴ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 የአውሮፓ ህብረትና የፈረንሳይ መንግሥት ለደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ80 ሚሊዮን ብር የጋራ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።

የአውሮፓ ህብረት ልዑክ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ዋና ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ የተለያዩ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት ህብረቱ ይደግፋል።

ህብረቱ ለተለያዩ ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል 300 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 80 ሚሊዮን ብር ለደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ነው ብለዋል።

የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክቱ ዛሬ ይፋ መደረጉንና ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

”ሆስፒታሉ በተሻለ መንገድ ለህብረተሰቡ በቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ድጋፍ እናደርጋለን” ነው ያሉት ።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው መንግሥታቸው በጦርነቱ የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬሚ አክለውም ዛሬ ይፋ የሆነው የደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት  የድጋፉ አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት የአውሮፓ ህብረትና የፈረንሳይ መንግሥት እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም፣ የህክምና ቁሳቁስና መድኃኒት ድጋፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የደሴ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኃይማኖት አየለ እንደሚሉት በፕሮጀክቱ የፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ፣ በጦርነቱ የተጎዱ የሆስፒታሉን ህንጻዎችን ማደስ፣ የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላትና ሌሎችም ይገኙበታል።

ፕሮጀክቱን አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ሆስፒታሉን በተሻለ ደረጃ መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።