የካንሰር ህክምና የጨረር ማሽን እጥረት ለእንግልት እንደዳረጋቸው በጅማ የካንሰር ህክምና ማዕከል ታካሚዎች ተናገሩ

237

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 የካንሰር ህክምና የጨረር ማሽን እጥረት ለእንግልት እንደዳረጋቸው በጅማ የካንሰር ህክምና ማዕከል ታካሚዎች ተናገሩ።

ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ያሉትን ማሽኖች በመጠገን ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ የሀዋሳውና የጎንደሩ የካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከላት በቅርቡ ወደ ስራ ስለሚገቡ የጅማውን ማዕከል ጫና እንደሚያቃልለው ምላሽ ሰጥቷል።

እየተስፋፉ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል የካንሰር በሽታ አንዱ ሲሆን የህክምናው ፈላጊዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ከጎረቤት ሀገራትም ጭምር የሚመጡ መሆኑን የጅማ የካንሰር ህክምና ማዕከል መረጃ ያሳያል።

ለህክምና ከጋምቤላ የመጡት ወይዘሮ በላይነሽ በቤንቶ እንደሚሉት ህክምናውን ለ23 ቀናት ወስደው ሲሻላቸው ወደ ቤት መመለሳቸውን ይናገራሉ።

ይሁንና ለክትትሉና ለማጠናቀቂያ ህክምና ወደ ማዕከሉ ተመልሰው ሲመጡ ያጋጠማቸው ወረፋ ለእንግልት እንደዳረጋቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በጨረር ህክምናው የብዙ ጊዜ ሲቃዬን ተገላግያለሁ የሚሉት ታካሚዋ፤ ለመጨረሻው ህክምና ተመልሼ ስመጣ ወረፋው ከበፊቱ ብሶ ጠበቀኝ ነው ያሉት።

አቶ መሀመድ ሀሰን ደግሞ ልጃቸውን ሊያሳክሙ ከሀረር የመጡ ተገልጋይ ሲሆኑ ከአንድ ወር በላይ ወረፋ ለመጠበቅ ተገደጃለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ህክምናውን ማግኘት ቀላል አይደለም ያሉት አቶ መሀመድ፤ በተለይም ከሩቅ አካባቢ የመጣን ሰዎች እዚህ ለመቆየትም ለመመላለስም ስለምንቸገር ህክምናውን በተቻለ ፍጥነት ማግኘት ብንችል ጥሩ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከ1 ዓመት በፊት ስራ የጀመረው የካንሰር የጨረር ህክምና መስጫ ማእከል የህክምናው መስጫ ማሽን አንድ ብቻ በመሆኑ ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ አሰቸጋሪ መሆኑን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የጤና ኢንስቲትዩት የካንሰር ማእከሉ ሃላፊ ዶክተር አማረ አሰፋ እንዳሉት ማእከሉ ህክምናውን ከጀመረ 14 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በቀን ሰላሳና አርባ ሰው በማከም የጀመረው የጨረር ማሽን አሁን ላይ በቀን እስከ መቶ ሰው ድረስ አያከምንበት ነው ብለዋል።

ከጨረር ማሽን እጥረቱ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት በተቋም ደረጃ ለመግዛት ውድ መሆኑን ጠቅሰው ተጨማሪ ማሽኖች ቢኖሩ የበርካታ ወገኖችን ህመም መፈወስ ይቻላል ብለዋል።

በህክምና ማእከሉ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረገው ህክምና ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማከም የቻለ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አማረ፤ ህክምናው ድግግሞሽ የሚፈልግ በመሆኑ አንድን የካንሰር ታማሚ ለማከም ከአንድ እስከ ሰላሳ ሶስት ቀን ሊቆይ ይችላል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጤና ኢንስቲትዩት ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ፈትያ አወል በበኩላቸው የህክምና ማእከሉ ሲጀምር በነጻ ሲሰጥ የነበረው የካንሰር ህክምና አገልግሎት ህክምናም ሆነ መድሃኒቱ ውድ በመሆኑ  አሁን ላይ አቅም ያላቸው ከፍለው እንዲታከሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ፈትያ አክለውም ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ የማሽኑ ቴክኒሻኖችና ሀኪሞችን በመቀናጀት በሶስት ሺፍት እየተሰራ መሆኑን አንስተው የማሽኑ ከህክምናው ፈላጊ ተገልጋይ ጋር ያለመጣጣም ችግር ስላለ ተጨማሪ ማሽን የሚገኝበትን ሁኔታ እያፈላለግን ነው ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የካንሰር ቁጥጥርና መከላከል ፕሮግራም አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ የካንሰር ማከሚያ የጨረር ማሽኑን በአገር አቀፍ ደረጃም እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።

ሆኖም በሁሉም ማእከሎች በብልሽት ምክንያት የቆሙትን በመጠገን ወደ ስራ የማስገባቱ ስራ እናካሄዳለን ያሉት አማካሪው፤ ተጨማሪ ማሽኖችንም ለማግኘት ከተባባሪ ተቋማት ጋር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከጅማው የካንሰር የጨረር ህክምና ማእከል በተጨማሪ ሁለት የህክምናው መስጫ ማዕከላት የሀዋሳውና የጎንደሩ በቅርቡ ስራ የሚጀምሩ በመሆናቸውም የጅማውን የወረፋ ጫና ያቃልላል ብለዋል ዶክተር ኩኑዝ።

በመሆኑም ህክምናውን የሚፈልጉ ታካሚዎች ወደሚቀርባቸው ማእከላት ሄደው መታከም እንደሚችሉ ገልዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም