የኢትዮ ኬኒያን የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተካሄደ

100

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 21/2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኬንያ የውጭ እና የዳያስፖራ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አልፍሬድ ሙቱዋ ጋር የኢትዮጵያንና ኬኒያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ምክክር አካሄዱ።

48ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ስብሰባም በዛሬው ዕለት በሱዳን ካርቱም መካሄድ ጀመሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአዲሱ የኬንያ የውጭና የዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር አልፍሬድ ሙቱዋ ጋር በካርቱም ተነጋግረዋል።

በሱዳን ርዕሰ-መዲና ካርቱም ውስጥ እየተካሄደ ካለው የኢጋድ ስብሰባ ጎን ለጎን ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቱን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

አቶ ደመቀ ኬንያ የሰላም ሂደቱ እንዲሳካ እንደ አገር እና በቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኩል ላደረገችው አስተዋፅኦ አመስግነው ለስምምነቱ ተፊፃሚነት መንግስት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

ዶክተር አልፍሬድ በበኩላቸው ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ወዳጅነት የተለየ ቦታ እንደምትሰጥና በሰላም ሂደቱ የነበራት ሚና የዚህ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚ መስክ በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የተሻለ ትብብር መፍጠር እንደሚችሉም መጥቀሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም