በደቡብ ክልል ሙስናን ለመከላከል ህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪ አቀረበ

100

ሀዋሳ ህዳር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ትግል ስኬታማ እንዲሆን መላው የክልሉ ህዝብ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ19ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ  የሚከበረውን  ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን  በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በኮሚሽኑ የሙስናና  ብልሹ  አሰራር  መከላከል  ዘርፍ  ምክትል  ኮሚሽነር  ፋሲካ ጌታቸው በመግለጫቸው የዘንድሮው ዓለም ዓቀፍ የፀረ ሙስና ቀን "ሙስናን መታገል በተግባር" በሚል መሪ ቃል ከህዳር 15 ቀን ጀምሮ በክልሉ በየደረጃው ባሉ አስተዳደሮች በተለያዩ ዝግጅቶች  እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመከላከልና በመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ከኮሚሽኑ ጎን እንዲሰለፍ ንቅናቄና ግንዛቤ መፍጠር  የበዓሉ ዋና ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

ሙስና በረቀቀ ስልት የሚፈፀም ወንጀል መሆኑንጠቁመው፤ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል  የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ  ሙስና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ተገንዝቦ ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፀረ- ሙስና ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን በብቃት መግታት እንዲቻል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር ባለፈው ዓመት ለ593 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠቱን ተናግረዋል።

ይህም ከእቃ ግዥ፣ ከሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ፣ ከከተማና ገጠር መሬት ምሪት፣ ከኮንትራት አስተዳደር፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥቆማዎች ወደ ኮሚሽኑ እንዲመጡ አስችሏል ብለዋል።

ጥቆማዎችን በማጣራት አብዛኛዎቹ  በዝግጅት ላይ እያሉ በማስቀረት 378 ሚሊዮን ብር የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ከምዝበራ ለማዳን መቻሉን አብራርተው በተቋማት ላይ በተጠና የአሰራር ሥርዓት ትግበራ በዓመቱ 39 ሚሊዮን ብር ከሙስና መታደግ እንደተቻለ ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ከሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘም ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ሀብታቸውን ማስመዝገባቸውን ገልጸው፤ 346 አስመዝጋቢዎችና ቤተሰቦቻቸው ያስመዘገቡት ሀብት ትክክለኛነት የማጣራት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ ሙሰኞችን በማጋለጥ የዕድገት ፀር የሆነውን ሙስና በመከላከል የዜግነት ግዴታውን በመወጣት ለሀገሩ ዕድገትና ብልፅግና በአንድነት እንዲረባረብ ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ  ጥሪ አቅርበዋል።

በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመው ብሄራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ የሚሰራ ክልላዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በቅርቡ እንደሚቋቋም አስታውቀዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም