የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ግብረ-ሃይል መቋቋሙን ኢንስቲትዩቱ ገለጸ

95

አዲሰ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 21/2015 በኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ግብረ-ሃይል ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የወባ መከላከያ መንገዶችን በመከተል ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት የመቀነስ ተግባር የህብረተሰቡ ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባልም ተብሏል።

በኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር መስፍን ወሰን ለኢዜአ እንደገለጹት የህብረተሰብ ጤና አደጋ በሆኑና በወረርሽኝ መልክ በሚከሰቱ በሽታዎች ላይ ቅኝትና የምላሽ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ለዚህም የአቅም ግንባታ ስራ፣ የቤተ-ሙከራ ስርዓት የመዘርጋትና የህብረተሰብ ጤና አደጋ መቆጣጠሪያ ማዕከላትን እስከ ዞን በመዘርጋት ጠንካራ የቅኝት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ በመከሰቱ ኢንስቲትዩቱ የቅኝትና ምላሽ ስራዎችን በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በየሳምንቱ የወረርሽኙን ስርጭትና አጋላጭ ሁኔታዎች በመተንተን የምላሽና የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል።

ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

በብሄራዊና በክልል ደረጃ በየሳምንቱ ግምገማ በማድረግና የፈጣን ምላሽ ቡድኑም በየቀኑ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረት አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶች እየተላኩ መሆኑንና የመከላከል ስራውም መቀጠሉን ገልፀዋል።

የፈጣን ምላሽ ግብረ-ሃይሉ በክልሎች ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ ህብረተሰቡን በማነቃነቅ፣ የጤና ባለሙያውን ግንዛቤ የበለጠ በማሳደግና የበሽታ መንስኤዎቹን በመለየት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በባለፈው ሳምንት የበሽታው ስርጭት ከቀደሙት ሳምንታት ጋር ሲነፃፀር የተወሰነ መቀነስ የታየበት መሆኑን አንስተው በቀጣይም ስርጭቱን የሚቀንሱ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም