የአማራ ክልል ምክር ቤት በኦዲት ግኝት መሰረት እርምጃ ስለመወሰዱ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገለጸ

131

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 21 ቀን 2015 የአማራ ክልል ምክር ቤት በኦዲት ግኝት መሰረት እርምጃ ስለመወሰዱ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገለጸ።

ጠንካራ የተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት በመንግስት መስሪያ ቤቶች በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጸመውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ፈጥኖ ማስተካከል እንደሚገባም የምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል።

የምክር ቤቱ አባል አቶ አየነው ተመስገን እና ወይዘሮ ዝናሽ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ በመንግስት ተቋማት የሚታየው ሙስናና ብልሹ አሰራር እየተባባሰ መጥቷል።

መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ የተሸጠ ቤት ስም ዝውውር፣ የማዘጋጃ ቤት ፋይል ማውጣትና ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶች ህዝቡ እስኪያውቀው ድረስ ተመን ወጥቶላቸው የሙስና ምንጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ብልሹ አሰራርና የስነ ምግባር መጓደል በጊዜው መታረም ባለመቻሉና እየተለመደ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ህዝቡ የመንግስት አገልግሎትን በነጻ የሚያገኝ መሆኑን እስከ መርሳት አድርሶታል ብለዋል።

ይሄን መሰረታዊ ችግር በጊዜ መቅረፍ ካልተቻለ ለስርዓቱ አደጋ መሆኑ የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ ምክር ቤቱ የእርምት አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል።

በኦዲት ሪፖርት የቀረበው የሙስናና ብልሹ አሰራር ግኝት ከችግሩ ስፋት አንጻር አመርቂ እንዳልሆነ አመልክተው፤ በከተማ መሬት፣ በኮንስትራክሽን፣ በመንግስት ግዥና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ ዝርፊያና ስርቆት በስፋት የሚፈጸምበት ሁኔታ መኖሩን  ጠቁመዋል።

የተዘረፈው ገንዘብ መልሶ በህዝቡ ላይ የሚፈጥረው አለመረጋጋትና የመልካም አስተዳደር ችግር የከፋ መሆኑንም አመላክተዋል።

በዚህም ምክር ቤቱ ለሙስናና ብልሹ አሰራሮች የሚያጋልጡ አሰራሮችን በመፈተሽ፣ ህዝቡን በማንቃት፣ አስፈጻሚ አካሉ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሚናውን መወጣት እንዳለበት ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በኦዲት ግኝት የቀረበው መረጃ በባለሙያዎች የተረጋገጠ በመሆኑ ተአማኒነቱ እንደማያጠራጥር ገልጸው፤ በዚሁ መሰረት አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኦዲት ግኝቱ ምክር ቤቱ ያለውን የህዝብ ውክልና በአግባቡ ተጠቅሞ በየጊዜው የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችንና ስርቆቶችን ለማስወገድ አጋዥ መሳሪያ እንደሚሆነውም ተናግረዋል።

የአስፈጻሚ አካሉ የቀረበውን ማስረጃ በመጠቀም ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱም በዚህ ረገድ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በምክር ቤት አባላት እየተነሱ ያሉ ችግሮች አመራሩ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ተገልጋዩ ማህበረሰብ ያለበትን ችግር የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

የህዝብ ሃብትና ንብረትን ያለአግባብ በመጠቀም፣ በመዝረፍና በመስረቅ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን አስገንዝበዋል።

ሙስና የሚፈጸመው በረቀቀ መንገድና መረጃን በማጥፋት በመሆኑ ሁሉም አካል ራሱን ከብልሹ ድርጊት በመጠበቅ አጥፊዎችን በመታገል የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

ህዝቡ የሰረቀንና የዘረፈን እንደ ጀግና ከመቁጠር አስተሳሰብ ወጥቶ የትግሉ አጋዥ እንዲሆን የጠየቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት የሚፈጸሙ የሙስና ድርጊቶችንና ብልሹ አሰራሮች ላይ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ አቋም መውሰዱን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሁለት ቀን ቆይታው የተለያዩ ሪፖርቶች ላይ በመምከር ለአስፈጻሚ አካላትና ለወረዳ ዳኝኞች ሹመት በመስጠት መጠናቀቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም