የ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተለዩ ጉዳዮች

484

በኳታር አስተጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ 10ኛ ቀኑን አስቆጥሯል። በዚህ ዋንጫ ከቀደሙት የተለዩ ክስተቶች ፣ ነባርና አዳዲስ ከዋክብት፣ ቴክኖሎጂና መሰል ጉዳዮች በስታዲየሞችና ከስታዲየም ውጭ መታየታቸው አልቀረም፡ እየታዩም ይገኛሉ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ይሄ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻቸው አለያም የመጀመሪያቸው የሆኑ ታዋቂና እንግዳ ከዋክብትም ከተመልካቾቻቸው እይታ አልራቁም። በዚህ የዓለም ዋንጫ በልዩነት ከሚጠቀሱ ዋና ዋና ክስተቶች መካከል፦

  • የሊዮኔል ሜሲና የክርስቲያኖ ሮናልዶ የመጨረሻ ዓለም ዋንጫ መሆን

የእግር ኳስ ከዋክብቶቹ አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲና ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የዓለም ዋንጫቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ሁለቱ ኮከቦች በመጨረሻ ዓለም ዋንጫቸው ትልቁን ክብር ለማግኘት እየታተሩ ነው። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በጋና ላይ ያስቆጠራት ግብ በአምስት የተለያዩ ዓለም ዋንጫዎች ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያ ተጫዋች አድርጎታል። አምስተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን እያደረገ ያለው ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ኢራንና ሜክሲኮ ላይ ሁለት ግብ በማግባት በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ስምንት በማድረስ ከአርጀንቲና የቀድሞ ኮከብ ዲያጎ ማራዶና ጋር በዓለም ዋንጫ ለአገሪቷ ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ክብርን ተጋርቷል። ከክርስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ ማን ዋንጫውን ማን ያነሳ ይሆን? ቀሪው ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

  • በበጋ ወቅት የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ

ከ2022ቱ ውጪ ከዚህ ቀደም የተደረጉ 21 የፊፋ ዓለም ዋንጫዎች የተደረጉት እ.አ.አ. በግንቦት፣ሰኔ እና ሐምሌ ላይ ነው ። በኳታር በክረምት ወቅት ያለው ሙቀት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በሕዳርና ታህሳስ ወር እንዲደረግ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ወስኗል። ይሄም 22ኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ በበጋ ወቅት የተካሄደ የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ ያደርገዋል።

  • በአረቡ ዓለም የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ

የዘንድሮው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በአረቡ ዓለም የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ነው።

  • ውዱ ዓለም ዋንጫ

ኳታር ለ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት 220 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣች እየተገለጸ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 10 ቢሊዮን ዶላሩ ለሰባት አዲስ ስታዲየም ግንባታና ለእንድ ስታዲየም እድሳት ወጪ የተደረገ ነው። ቀሪው ለውድድሩ የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የዋለ ነው።

  • ሁሉም ስታዲየሞች የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ተገጥሞላቸው የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ

በኳታር ባለው ሞቃታማ የአየር ንብረት ምክንያት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስምንት ስታዲየሞች የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያ ተገጥሞላቸዋል። ይሄም ሁሉም ስታዲየሞች የአየር ማቀዝቀዣ ተገጥሞላቸው የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ አድርጎታል።

  • በፊፋ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ለውድድር የዋለ የመጀመሪያው ጊዜያዊ ስታዲየም

ኳታር ለዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ስምንት ስታዲየሞች ያሰናዳች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሰባቱ አዲስ ናቸው። አዲስ ከተገነቡት ስታዲየሞች መካከል ደግሞ ስታዲየም 974 ይገኝበታል። ስያሜያውን ያገኘው የተሰራው ድጋሚ ጥቅም ላይ ከዋሉ 974 የመርከብ ዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮች በመሆኑ ነው። በተጨማሪም የስታዲየሙ ስያሜ የኳታር የስልክ መለያ ቁጥር የሚጀመረው +974 ከመሆኑ ጋርም ይያያዛል። ኳታር ግንባታው እ.አ.አ 2018 ተጀምሮ እ.አ.አ 2021 የተጠናቀቀውን ስታዲየም የመርከብ እቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮችና መቀመጫዎች ዓለም ዋንጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሌሎች አገራት ለመሸጥ አቅዳለች። ይህም ስታዲየም 974 በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያ ጊዜያዊ ስታዲየም ያደርገዋል።

  • የፊፋ የዓለም ዋንጫ ያዘጋጀች ትንሿ አገር

እ.አ.አ በ2022 በወጣ መረጃ ኳታር 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕዝብ  በቆዳ ስፋቷም አነስተኛ (11 ሺህ 581 ካሬ ኪሎ ሜትር) አገር ናት። ይሄም በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ ኳታር ውድድሩን ካሰናዱ አገራት ትንሿ አገር ያደርጋታል።

  • ከካርቦን ነጻ የሆነ ዓለም ዋንጫ

ግንዛቤ፣ልኬት፣ቅነሳና ማብቃቃት በሚሉ አራት ደረጃዎች ኳታር የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ከካርቦን ነጻ ለማድረግ ተስፋ ሰንቃለች። አገሪቷ ይህንን እውን ለማድረግ ታዳሽ የኃይል መፍትሔዎች፣ ኃይልና ውሃ ቆጣቢ ስታዲየሞች፣ ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁሶችን እንደገና በመጠቀም እና ሁሉንም በካይ ጋዞች የሚያስወግድ አማራጮችን በመተግበር ላይ ነች።

  • ከፍተኛ ጥግግት ያለው ዓለም ዋንጫ

11 ሺህ 581 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ኳታር የዓለም ዋንጫውን የሚያስተናግዱ ስምንቱ ስታዲየሞቿ በ55 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ቡድኖች እና ደጋፊዎች በጨዋታዎች ወቅት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በረራ አያደርጉም ማለት ነው። ስታዲየሞቹ ያሉበት ቦታ ዓለም ዋንጫውን ከፍተኛ ጥግግት ያለው(በቅርብ ርቀት) የሚካሔድ ውድድር አሰብሎታል።

  • የመጀመሪያዎቹ ሴት ዳኞች በፊፋ ዓለም ዋንጫ

ብዙ የመጀመሪያዎች ያሉት 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዘንድሮ ሴት ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ያጫወቱበት ዓለም ዋንጫ ነው። ዓለም ዋንጫውን እንዲያጫውቱ ከተመረጡት 36 ዳኞች መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው። ሳላማ ሙካንሳንጋ ከሩዋንዳ፣ያሚሺታ ዮሺሚ ከጃፓን እና ስቴፋን ፍራፓርት ከፈረንሳይ በዓለም ዋንጫው እንዲያጫውቱ የተመረጡ ሴት ዳኞች ናቸው።

  • የ32 ብሔራዊ ቡድኖች ተሳትፎ ደህና ሰንብት የሚባልበት የዓለም ዋንጫ

እ.አ.አ በ1930 የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ በኡረጓይ አስተናጋጅነት ሲካሄድ 13 አገራት ብቻ ተሳታፊ ነበሩ። በሁለተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 16፣ እ.አ.አ 1982 በተካሄደው 12ኛው የዓለም ዋንጫ ወደ 24 እንዲሁም በፈረንሳይ አስተጋጅነት የተካሄደው 16ኛው የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ወደ 32 ከፍ ብሏል። በኳታር አስተጋጅነት እየተካሄደ ያለው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 32 ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት የውድድር ፎርማት ስንብት የሚያደርግበት ነው። እ.አ.አ በ2026 በካናዳ፣ሜክሲኮና አሜሪካ በጥምረት በሚሰናዳው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 48 አገራት ይሳተፋሉ።

  • በአጭር ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቀው የመጀመሪያው የፊፋ ዓለም ዋንጫ

  ለ28 ቀናት የሚቆየው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በዓለም ዋንጫ ታሪክ አጭር ቆይታ ያለው የዓለም ዋንጫ ነው።

  • በሁሉንም የዓለም ዋንጫዎች የተሳተፈች ብቸኛ አገር ብራዚል

ብራዚል የዘንድሮውን ጨምሮ በ22ቱም የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተሳተፈች ብቸኛ አገር ሆናለች። በተጨማሪም ብራዚል ውድድሩን አምስት ጊዜ ያሸነፈች ብቸኛ አገር ናት።

  • የዓለም ዋንጫ አምስት የአፍሪካ ተወካዮች በራሳቸው ዜጋ እየተመሩ የተሳተፉበት የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የዓለም ዋንጫዎች አፍሪካ አገራት በውጭ አገር አሰልጣኞች ላይ የነበራቸው ጥገኝነት በአፍሪካውያንና በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ሲያስተቻቸው ነበር። በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑት ጋና፣ካሜሮን፣ሞሮኮ፣ቱኒዚያና ሴኔጋል በራሳቸው አገር ዜጎች በመመራት አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል። ካሜሮን በሪጎበርት ሶንግ፣ ጋና በኦቶ አዶ፣ ሴኔጋል በአሊዩ ሲሴ፣ ሞሮኮ በዋሊድ ሬግራጉዊ እና ቱኒዚያ በጃሌድ ካድሪ እየተመሩ ነው።

  • ውዱ የስታዲየም ትኬት የተሸጠበት የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ

ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሉሳይል ስታዲየም ለሚደረገው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ትኬት ዋጋ 1 ሺህ 607 ዶላር (5 ሺህ 850 የኳታር ሪያል) ነው። ይህም በፊፋ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ውዱ የስታዲየም ትኬት ሽያጭ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም