በአማራ ክልል ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል በቁርጠኝነት ይሰራል--ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

165

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2015 በአማራ ክልል በተለያዩ ስልቶች የሚፈፀም ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል በተለየ ትኩረት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍለ አስታወቁ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት  በባህርዳር ከተማ  ለሁለት ቀናት ያካሄደው  6ኛ ዙር፣  2ኛ  ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ዶክተር አማረ ብርሃኑ የመስሪያ ቤታቸውን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ በዓመቱ በ12 መስሪያ ቤቶች ላይ የክዋኔ ኦዲት መከናወኑን ገልጸዋል።

በመስሪያ ቤቶቹ የፕሮጀክቶች መዘግየት፣ የመንግስት ሃብት ብክነት፣ የግዥ ስርዓት አለመጠበቅና ሌሎች ችግሮች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም በኦዲት ግኝቱ መሰረት መልስ ባለመስጠታቸው ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዶክተር አማረ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የቀረበን ሪፖርት ተከትሎ  እንዳሉት  የክልሉ ህዝብ በድህነትና በጦርነት ውስጥ ያለፈ እንደመሆኑ በልማትና መልካም አስተዳደር በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው።

"በነበረው ሂደት ሙስናና ሌብነት እየተንሰራፋና የችግሮች እየተደራረበ መምጣት ትልቅ ስጋት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም በልማት ፕሮጀክቶች መጓተት፣ በግዥ፣ በከተማ መሬትና በሌሎች ላይ የሚፈፀመው ስርቆትና ዘረፋ ዋናው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የህዝቡ የመልማት ፍላጎትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው" ያሉት ዶክተር ይልቃል የልማት ጥያቄውን ለመመለስ ሙስናና ሌብነትን መቆጣጠር ግዴታ መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስት ለሀገር ልማትና እድገት ፀር የሆነውን ሙስናን፣ ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን ለመግታት በቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ መወሰኑን አስገንዝበዋል።

"ሌቦችን በተጨባጭ ማስረጃ በማስደገፍ በህግ ተጠያቂ ለማድረግና ያለአግባብ የተወሰደ ገንዘብን በማስመለስ ላይ ያተኮረ ስራ በቅንጅት ይሰራል" ሲሉም አስታውቀዋል።

"አመራሩ፣ የመንግሥት ሰራተኛውና ህዝቡ የገጠመንን ተግዳሮት በመገንዘብ ሙሰኞችን እና ሌቦችን የመቆጣጠር ትግሉን በመደገፍ ሊያግዝ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የምክር ቤት አባላትም የክልሉ መንግስት የያዘውን አቋም አስመልክቶ ለህዝቡ ግንዛቤና መረጃ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም