አፍሪካውያን ግልጽና አካታች የዲጂታል ስትራቴጂ በመንደፍ አህጉራዊ ብልጽግናና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አለባቸው

234

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 አፍሪካውያን ግልጽና አካታች የዲጂታል ስትራቴጂ በመንደፍ ሁሉን አቀፍ አህጉራዊ ብልጽግናን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባቸው የዓለም አቀፉ የዲጂታል አካታችነት አጋርነት የአፍሪካ አስተባባሪ ኦኒካ ማካዋክዋ ተናገሩ።

አስተባባሪዋ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ዛሬ መካሄድ በጀመረው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ በከፍተኛ የዘርፉ መሪዎች ደረጃ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ነው።

በውይይቱ የኢንተርኔት ተደራሽነትን እውን ለማድረግ ያሉ ዕድሎች እና ፈተናዎች ተነስተው የመፍትሔ ሀሳቦች ተመላክተዋል።

ተሳታፊዎች የመሰረተ ልማት ችግር፣ የዲጂታል አጠቃቀም ክህሎት ክፍተት፣ የፋይናንስ እጥረትና ሌሎች ችግሮችን ከየሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ዘርዝረዋል።

በዓለም የዲጂታል ማህበረሰብ ውስጥ አካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችን፣ የገጠሩን ማህበረሰብ ክፍል፣ ስደተኞችን፣ ህጻናትን ያካተተ የኢንተርኔት ግንኙነት ስርዓት በመዘርጋት በኩል አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተነስቷል።

የዓለም የዲጂታል አካታችነት አጋርነት የአፍሪካ አስተባባሪ ኦኒካ ማካዋክዋ የዲጂታል አብዮት በጅማሬ ላይ ያለባት አፍሪካ ግልጽና አካታች ስትራቴጂን መንደፍ እንዳለባት አመላክተዋል።

በዚህም ሁሉን አቀፍ የሆነ ብልፅግናን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ በመጠቆም።

ከኢንተርኔት ግንኙነት ውጭ የሆኑ ዜጎችን በኢንተርኔት ማገናኘት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በጉባኤው የፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች የተለያዩ አሰራሮችን መተግበር፣ የግልና መንግስት አጋርነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑም ተነስቷል።

የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ባልቻ ሬባ የመንግስትና የግል አጋርነትን ማጠናከር፣ የተለያዩ የገንዘብ አማራጮችን መፈለግ፣ የዜጎችን አቅም ያገናዘበ ኢንተርኔት ማቅረብና ሌሎች የመፍትሔ ሀሳቦችን አመላክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንሁዋ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሀገራት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሚቀርጹ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ የዲጂታል አካታችነትን ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የማይበገር የበይነ መረብ ግንኙነት መሰረተ-ልማት መገንባት የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዋነኛ ተግባር ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

“የማይበገር ኢንተርኔት ለዘላቂና እኩል የጋራ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል እየተካሔደ በሚገኘው ጉባኤ የዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል።

በጉባኤው ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ3 ሺህ በላይ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ጉባኤው በነገ ውሎው በይነ መረብን በአግባቡ ማስተዳደር፣ ደህንነትና ተጠያቂነትን ማስፈን በሚሉና ተያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ይሆናል።

የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ልማትና ተወዳደሪነትን በቀጣይነት የሚያረጋግጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን መቅረጽና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የጉባኤው አላማ ነው።