የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

359

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተካሔደው የ12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ ቋሚ ኮሚቴው እውቅና የሚሰጠው ስኬት ነው ብለዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር አሁን ላይ አሰራሩን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት እንዲያሳካ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።

ከዚህ ጎን ለጎንም በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ነገሪ ያሳሰቡት።

በአሁኑ ወቅት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚኒስቴሩ እየተካሔዱ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም እንዲሁ።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ አገዝ የማድረግ ሂደት በጥብቅ ድጋፍ እና ክትትል ሊከናወን እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው፤ በቅርቡ የተካሔደው 12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደት በርካታ ጥቅምና ልምድ የተኘበት መሆኑን ናግረዋል።

ፈተና አሰጣጡ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩ የቀየረ በመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ የተሻሉ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በመላ ሀገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ከ47 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የንቅናቄ ስራዎች መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፤  በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሙከራ ደረጃ መተግበር መጀመሩን ነው ያነሱት።

የትምህርት ምዘና አገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድም ስኬታማ የተባሉ ስራዎች መከናወናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቅሰዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ መምህራን ለትምህርት ጥራት እና እድገት ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸው ጠቁመው መምህራን የሚያነሷቸውን  ጥያቄዎች  ለመፍታት ከመምህራን ማህበር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አንዱ እርምጃ በመሆኑ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን መጀመሩን ነው የገለጹት።

በመሆኑም ከ2015 ዓ.ም ሰኔ ወር ጀምሮ በመደበኛና በተከታታይ በመንግስትና በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱም  ተናግረዋል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ የማድረግ ሂደትም ከአምስት በማይበልጡ የትኩረት መስኮች ልየታ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 23 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ትምህርት ላይ እንደሚገኙም በሪፖርቱ ተመላክቷል።