የጋምቤላ ክልል ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በማጠናከር የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ ገለጸ

152

ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 የጋምቤላ ክልል ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በማጠናከር የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

‘‘ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላም’’ በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ ክልል ደረጃ 17ኛው የብሄር ብሔረሰቦች ቀን በማስመልከት ሲምፖዚየም ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም የብሄር ብሄረሰቦችና የህዝቦችን ብዝሃነት፣ ማንነት፣ እኩልነትና ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያረጋግጥ ስርዓት መሆኑንም አስታውሰዋል።

ይህም በመሆኑ ክልሉ የብሄር ብሔረሰቦችን እኩልነት ያረጋገጠውን ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን በመጠናከር የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ይሰራል ብለዋል።

ስርዓቱን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥና የታለመውን የልማት ግብ ለማሳካት በአንድነት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ትሁት ሐዋሪያት በበኩላቸው በህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመካከላቸው ያለውን የአብሮነት እሴት ያጎለብቱበታል ብለዋል።

ከዚህም አልፎ በብዝኃነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን በማጠናከር ሕዝቡ ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፍ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበሩ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በህገ-መንግስትና በፌዴራሊዝም ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ስርዓቱ እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ ያስችላልም ብለዋል።

በሲምፖዜየሙ ላይ የክልሉ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉ ሲሆን ሁለት የመወያያ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በክልል ደረጃ 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በነገው ዕለት በጋምቤላ ስታዲየም በተለያዩ መርሓ ግብሮች እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም