ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት አርአያ ሆነው ሊሰሩ ይገባል

170

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት አርአያ ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኢትዮጵያ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ዛሬ በፓናል ውይይት አክብሯል።

የቢሮ ኃላፊው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ትምህርት ቤቶች ህብረ-ብሔራዊ አንድነት በትውልዱ ልቦና ውስጥ እንዲሰርጽ በሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና አላቸው።

የትምህርት ዘርፉ ትውልድ የሚታነጽበት ማዕከል በመሆኑ በዘላቂ የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፉ የእውቀት ማዕከል በመሆኑ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ጽኑ መሰረት እንዲይዝና የውይይት ባህል እንዲዳብር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የትምህርት ማህበረሰቡ በህገ-መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ የበዓሉ መከበር ደግሞ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

አገራዊና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያስችላሉ የተባሉ ሃሳቦች በፓናል ውይይቶቹ መዳሰሳቸውን ገልጸዋል።

ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን "የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላም " በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29 ቀን በሐዋሳ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም