በግብርና ዘርፍ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የተቀናጀ አሰራር ያስፈልጋል - ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ዘርፍ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የተቀናጀ አሰራር ያስፈልጋል - ተመራማሪዎች

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በግብርና ዘርፍ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ተመራማሪዎች አመለከቱ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ "ሳይንስ ለምግብ ዋስትና እና ሉአላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ አራተኛው የሳይንስ ሳምንት አካሂዷል።
በሳምንቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ስርፀት ዳይሬክተር ዶክተር ሀብታሙ ተመስገን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሳይንስ ለምግብ ዋስትናና ሉአላዊነት ሚናው የጎላ ነው።
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ልማት በተለይም በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ እየተሰራ ያለው ስራ በሳይንሰና ቴክኖሎጅ መደገፍ እንዳለበት አመልክተዋል።
ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታን መቋቋም የሚችል የግብርና ልማት ለማረጋገጥና የአፈርና ውሃ አጠቃቀምን ለማሻሻል ምርምር መካሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ተመራማሪዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ምርምሮችን አጽንኦት ሰጥተን በመስራት በዘርፉ የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግር መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ከበደ አበጋዝ በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ልማት እያደረገች ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
ይህንን ጥረት በሳይንስና ቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በግብርና ዘርፍ የተደረጉ ጠቃሚ ሳይንሳዊ ምርምሮች ወደ መሬት ወርደዉ የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ምሁራን፣ መንግስትና ኢንዱስትሪው በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል።
በግብርና ልማቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርና ሳይንሳዊ ምርምሮች ከአካባቢው ማህበረሰብ ባህል፣ ልማድና አኗኗር ጋር በማሰናሰል እንዲሁም የማህበረሰብን ዕውቀት በመጋራት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በበኩላቸው በሀገራችን አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችንና ለም መሬት ይዘን የምግብ ዋስትናችንን ባለማረጋገጣችን ለተለያዩ ተጽኖዎች ተጋላጭ ሆነናል ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።