በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት የተዘጋጁ ከ944 ሺህ 880 በላይ መጽሐፍት ታትመው በመሰራጨት ላይ ናቸው

258

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት የተዘጋጁ ከ944 ሺህ 880 በላይ መጽሐፍት በሀገር ውስጥ ታትመው በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ የ2015 የትምህርት ዘመን አጀማመር ሪፖርትን ለክልሉ ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ በርካታ ትምህርት ቤቶች በቂ መሰረተ-ልማት ያልተሟላላቸውና ከደረጃ በታች ናቸው።

በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ባለድርሻ አካላት ዘርፉን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

የትምህርት ቤቶችን መሰረተ-ልማት በማሟላት ገጽታቸውን መቀየር ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ  አመት 5 ሺህ 358 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ማቅረብ ላልቻሉ ተማሪዎች ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ እርሳስና ዩኒፎርም መሰራጨቱን ገልፀዋል።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት የተዘጋጁ ከ944 ሺህ 880 በላይ መጽሐፍት በሀገር ውስጥ ታትመው እየተሰራጩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በውጭ ሀገር የታተሙ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት ደግሞ በማጓጓዝ ሂደት ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

በትምህርት ተቋማት ለተከናወኑ ተግባራት ከህብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት ከ314 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተው፤ አሁንም ቀሪ ስራዎች በመኖራቸው የጋራ ርብርቡ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የምክር ቤት አባላትም በጦርነቱ የተጎዱና ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ህዝብን በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማትና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት በወቅቱ ታትሞ አለመድረስ ለመማር ማስተማር ስራው እንቅፋት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አሁንም በፍጥነት መሰራጨት እንደሚገባው አመልክተዋል።

በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ መምህራን የስነ-ልቦና ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።