በሐረሪ ክልል የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቋመ

115

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የሙስና ወንጀልን ለመከላከል እና የወንጀሉን ተዋንያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ክልላዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ይህ ኮሚቴ በተለያዩ መዋቅሮች በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም የመሬት ነክ ሙስና፣ ከግብር፣ ከግዥ፣ ለፕሮጀክቶች፣ ከግንባታ ፍቃድ፣ ከመንጃ ፍቃድ ህገ ወጥ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ለመንግስታዊ አገልግሎቶች ከዜጎች የሚጠየቅ ጉቦ፣ በፍትህ ዘርፍ እና በሌሎችም ዘርፎች የሚፈፀም ሙስናን በመከላከል ወንጀለኞች ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው።

አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴው በሙስና ወንጀል ላይ የሚያደርገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ የሚያስተባብር፣ የወንጀሉን ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ነው።

የኮሚቴው አባላትም፦

1ኛ.አቶ አዩብ አህመድ__የሀረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ

2ኛ.አቶ ካሊድ ኑሬ__ የሀረሪ ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

3ኛ.አቶ ጥላሁን ዋደራ____ የሀረሪ ክልል ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ

4ኛ.አቶ ከተማ ለማ___ የመልካም አስተዳድር እና ሪፎርም አማካሪ

5ኛ.አቶ ሐምዲ ሰልሃዲን_ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አማካሪ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ኮሚቴው የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንዲችል የህብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።

በቀጣይም ኮሚቴው ይፋ በሚያደርጋቸው አድራሻዎች ህብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ በመላክ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

ክልላዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸው እርምጃዎችና የእንቅስቃሴው ውጤትም በየጊዜው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም