ህዝቡን ከፀጥታ ስጋት ለማላቀቅና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው _ ዶክተር አለሙ ስሜ

210

ህዳር 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ህዝቡን ከፀጥታ ስጋት ለማላቀቅና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለፁ ።

አርሶ አደሩ በአንድ እጁ ሰላም የሚነሳውን አሸባሪውን ሸኔ እየተፋለመ በሌላው እጁ ልማቱን በማስቀጠል ድርብ ጀግንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

ዶክተር አለሙ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ከዶኒ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ያወያዩ ሲሆን በዞኑ ቦሶት ወረዳ ቆምቤ ጉግሳ ቀበሌ በክላስተር የለማ የአርሶ አዶሮች የፓፓያ ማሳም ጎብኝተዋል::

በውይይቱ ላይ ዶክተር አለሙ እንደገለፁት ህዝቡ ልማቱን በተረጋጋ መልኩ ለማከናወን እንዲችል ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ የመንግስት ትኩረት ነው ።

ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ አለኝ የሚልና ይሄንንም በሰላማዊ መንገድ የሚያራምድ አካልን ለማስተናገድ መንግሥት መዘጋጀቱን ጠቁመው ጸጥታን በማወክ በቦሰትና ፈንታሌ ወረዳ የሰላም ስጋት የሆነውን የሸኔን ጥቃት ማስወገድ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ሲሰቃይ ሲገደልና ሀብቱ ሲዘረፍ ያልነበረው ሸኔ፣ የኦሮሞ ህዝብና ከአብራኩ የወጡ ቄሮዎችና ቀሬዎች በባዶ እጃቸው ታግለው ያስገኙትን ድል ለመቀማት ዛሬ ላይ ነፃ አውጪ መሆን አይችልም ብለዋል ።

የደም ነጋዴዎች መጨረሻቸው መጥፋት ነው ያሉት ዶክተር አለሙ፣ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ከጥፋት ቡድኑ ጋር የተሰለፉ አካላት በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ህዝቡ ተደራጅቶ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት የገለጹት ዶክተር አለሙ፣ ለሌባና ዘራፊ ስንቅና መረጃ የሚያቀርቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

በህብረተሰቡና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ መረጃ ሰጪዎችን ጭምር የማጥራት ስራ በዘላቂነት ይሰራል ብለዋል ።

በውይይቱ የተሳተፉ የዶኒ ፣ ቦፋ፣ ቦሌ ፣ ኑራ ሄራ ነዋሪዎች ፀረ ሰላም ሃይሎችን ለማስወገድ መንግስት የሚያደርገውን ህግ የማስከበር እርምጃ በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የህዝብ ውይይቱን ተከትሎ ዶክተር አለሙ፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሶት ወረዳ ቆምቤ ጉግሳ ቀበሌ በክላስተር የለማ የአርሶ አዶሮች የፓፓያ ማሳ ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት እንደገለፁትም አርሶ አደሩ በአንድ እጁ ሰላም የሚነሳውን አሸባሪውን ሸኔ እየተፋለመ በሌላው እጁ ልማቱን በማስቀጠል ድርብ ጀግንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ሙሉ አቅሙንና ጉልበቱን በልማቱ ላይ እንዲያውል መንግሥት ህግ የማስከበርና ሰላም የማስፈን ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል ።

በተለይ በአካባቢው የሚስተዋለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር የልማቱ ትልቁ እንቅፋት መሆኑን የገለፁት ዶከተር አለሙ፣ መንግስት የፀጥታ ችግሩን ከምንጩ በማድረቅ ህዝቡ በልማቱ ላይ እንዲያተኩር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክላስተር የለማው ፓፓየ አርሶ አደሩ በፀጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ ያሳየው የአይበገሬነት ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል ።

መንግሥት የአትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የጀመረው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው አርሶ አደሩም የውጤቱ ተቋዳሽ እየሆነ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም