በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 4 ወራት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል-ቢሮው

150

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አራት ወራት በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮችና በክልሉ መንግሥት የአራት ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ በሰጠው መግለጫ በክልሉ ሕግ ማስከበርን ጨምሮ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አመልክቷል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ሀይሉ አዱኛ በመግለጫቸው የክልሉ መንግስት ባለፉት አራት ወራት ከመደበኛና ማዛጋጃ ቤታዊ የገቢ ምንጮች 22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል ብለዋል።

በምርት አሰባሰብ ሂደትም ባለፈው መኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን በ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 500ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱንና እስካሁን 278 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ተመርተው ወደ ውጪ ከሚላኩ ምርቶች መካከል አንዱ የአቮካዶ ምርት መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ከተሰበሰበው ምርት 38 ቶን አቮካዶ ለውጪ ገቢያ መቅረቡንም ተናግረዋል።

በክልሉ ከተመረተው ቡና ከ200 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገቢያ መቅረቡን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸው፤ ከ4 ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

የክልሉን የአደጋ መከላከል አቅም ለማጎልበትም በቡሳ ጎኖፋ ቢሮ በኩል የገቢ ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ለችግር የተጋለጡ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መደገፍ እንደተቻለም አስረድተዋል።

ከዚህም ባሻገር መንግሥት በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።

መንግሥት በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን እያከናወነ ያለውን ሕግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠው የክልሉ ሕዝብ ከፀጥታ አካላት ጎን ሆኖ ድጋፍና ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሰላሙን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም