በዓለም ዋንጫው ያልተጠበቁና ያልተገመቱ ውጤቶች

357

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ውድድር ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል።

በዓለም ዋንጫው ያልተጠበቁና ያልተገመቱ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው።

ትናንት በአል ቱማማ ስታዲየም ሞሮኮ በቱርኩ ቤሺክታሽ ክለብ የሚጫወተው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ሮሜን ሳይስ እና የፈረንሳዩ ቱሉዝ የፊት መስመር ተሰላፊ ዘካሪያ አቡላል ባስቆጠሯቸው ግቦች ቤልጂየምን 2 ለ 0 ረታለች።

በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 22ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የአትላስ አንበሶች ያስመዘገቡት ውጤት የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያስገረመ ነው።

ኬቨን ደብሮይን፣ ኤደን ሀዛርድና ኤክሰል ዊትስልን ጨምሮ ወርቃማው የእግር ኳስ ስብስብ ይዟል በሚል የተነገረለት የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ጠንካራ ፍልሚያ ባደረገው ሞሮኮ ተሸንፏል።

ቤልጂየም በወቅቱ የፊፋ አገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮ ነጥቧን ወደ አራት ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ ነጥብ በሰበሰበችው ክሮሺያ በግብ ክፍያ ተበልጣ በምድብ ስድስት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በአንጻሩ ቤልጂየም ከምድቧ የማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ የገባች ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ለመሻገር በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ክሮሺያን ማሸነፍ ግድ ይላታል።

በምድብ ሶስት ሳዑዲ አረቢያ አርጀንቲናን 2 ለ 1 ያሸነፈችበት ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያስገረመ ውጤት ነበር።

ውጤቱ በአርጀንቲና ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 51ኛ ላይ የምትገኘው ሳዑዲ አረቢያ ከመመራት ተነስታ ከዓለም ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን አርጀንቲናን ነው ያሸነፈችው።

አርጅንቲና በመጀመሪያው አጋማሽ ሊዮኔል ሜሲ በፍጹም ቅጣት ባስቆጠራት ግብ መሪ የነበረች ቢሆንም ሳሌህ አልሼሪና ሳሌም አልዳውሳሪ ከእረፍት መልስ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሳዑዲን አሸናፊ አድርጓታል።

የሳዑዲ አረቢያ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ከጨዋታው በፊት “ኳታር የመጣነው ለመዝናናት ሳይሆን ለፉክክር ነው፤ እኛ ተፎካካሪ ነን” የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር።

ውጤቱም ይሄንን የሚያሳይ ነው ማለት ይቻላል።

በብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን በኩል ውጤቱ የእግር ኳስን የማይገመት ባህሪይ የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ሳዑዲ አረቢያ በምድብ ሁለተኛ ጨዋታዋ በፖላንድ 2 ለ 0 መሸነፏ ይታወቃል።

በምድብ አምስት ጃፓን የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋን ጀርመንን 2 ለ 1 ያሸነፍበት ውጤትም ብዙዎች ያልጠበቁት ውጤት ነበር ማለት ይቻላል።

ጀርመን የማንችስተር ሲቲው የአማካይ ተጫዋች ኢልካይ ጉንዶጋን በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ 1 ለ 0 የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት ማጠናቀቅ ችላ ነበር።

በሀጂሜ ሞሪያሹ የሚመራው የጃፓን ብሔራዊ ቡድን በጀርመን ቡንድ ስሊጋ ለፍራይቡርግና ለቦኸም የሚጫወቱት ሪትሱ ዶዋንና ታኩማ አሳኖ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሰማያዊዎቹ ተዋጊዎች (The samurai blue) 2 ለ 1 አሸናፊ አድርገዋል።

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን “በጀርመን ሊግ የሚጫወቱት ጃፓናውያን ተጫዋቾች ጀርመንን ጉድ ሰሩ” በሚል ርዕስ ሲዘግቡ ነበር።

የመጀመሪያ ጨዋታዋ በእንግሊዝ 6 ለ 2 የተሸነፈችው ኢራን ዌልስን 2 ለ 0 በማሸነፍ ያስመዘገበችው ውጤት ያልተጠበቀ ነበር።

የኢራን ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ውስን የማይባሉ ግልጽ የግብ እድሎችን መፍጠር ችሏል።

ሩዝቤህ ቼስሚና ራሚን ሬዛያን የመደበኛ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይ ያስቆጠሯቸው ግቦች ኢራንን 2 ለ 0 አሸናፊ ያደረገ ሲሆን በአንጻሩ በሮብ ፔጅ የምትሰለጥነውን ዌልስ ልብ የሰበረ ነው።

ፓርቹጋላዊው የኢራን አሰልጣኝ ካርሎስ ኪዬሮዥ ከዌልሱ ጨዋታ በፊት በሰጡት አስተያያት” የኛ ዓለም ዋንጫ የሚጀምረው ዛሬ ነው” የሚል ነበር።

ኢራን ሶስት ነጥብ በማግኘት ወደ 16ት ውስጥ የመግባት እድሏን ያለመለመለች ሲሆን በቀጣይ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

በምድብ አምስት በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ 7 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት የተሸነፈችው ኮስታሪካ ትናንት በአህመድ ቢን አሊ ስታዲየም ጃፓንን 1 ለ 0 መርታቷ ያልተጠበቀ ውጤት ነበር።

በሉዊስ ፈርናንዴዝ ሉዊስ የምትመራው ኮስታሪካ በመጀመሪያው ጨዋታ የተወሰደባት ብልጫ በሁለተኛውም ጨዋታ ተሸንፋ ከውድድሩ ትሰናበታለች የሚሉ ግምት ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ሲሰጥ ነበር።

ይሁንና በኮስታሪካ የእግር ኳስ ሊግ ለስፖርት ሄሬዲያኖ ክለብ የሚጫወተው የቀኝ መስመር ተጫዋች ኬይሸር ፉለር በ81ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ሎስ ቲኮስ (የኮስታሪካ ተወላጅ የሚጠራበት ስም ነው) ጃፓንን አሸንፈዋል።

ኮስታሪካ ከጀርመን ጋር በምታደረገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እጣ ፈንታዋን ትወስናለች።

በስምንት ስታዲየሞች ከሕዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በቀጣይ ምን ያሳየን ይሆን?።