ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል-የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ

448

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19/2015 ከኦሮሚያ ክልል በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታወቀ።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በክልሉ የተከናወኑ የተለያዩ ተግባራት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የክልሉ መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ባለፈው አመት ህዳር ወር ከድሬዳዋ ተረክቦ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በማዘዋወርና የገቢ ማሰባሰብ ሁነቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

ዋንጫው በክልሉ ባደረገው የአንድ ዓመት ቆይታ የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በስጦታ፣ በቦንድ ግዢ እና በአጭር መልእክት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ዋንጫው በክልሉ ያለውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ሲዳማ ክልል ለመሸኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ ሀላፊው በክልሉ ባለፉት አራት ወራት በመደበኛና በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል ነው ያሉት።

እስካሁን 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን እንዲሁም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም 278 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤት ምገባ እና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ አበረታች ስራ መሰራቱን አንስተዋል።