17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀመረ

595

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 19/2015 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤውም ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ተወካዩች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን “ለዲጅታል አካታችነት መሰረተ ልማት መልካም ተሞክሮዎችና ምክረ ሀሳቦች” በሚል ሃሳብ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያን ተሞክሮ ያቀረቡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለኢንተርኔት መሰረተ ልማት መስፋፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ለዜጎች የኢንተርኔት ተደራሽነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አስታውቀው፤ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው መስራት ለሚፈልጉ አካላት ጥሪ አቅርበዋል።

የ17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ዋናው መክፈቻ በነገው እለት እንደሚካሄድ ተነግሯል።

የዓለምን የምጣኔ ሀብት እድገትና የሰዎችን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ካቀላጠፋት ጉዳዮች አንዱ የኢንተርኔት ተደራሽነት ሲሆን ዘርፉን በባለቤትነት በመምራት ለዓለም ህዝብ ጥቅም እንዲሰጥ በማሰብ የኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም ከ17 ዓመት በፊት እንዲመሰረት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተጀመረው 17ኛው ጉባኤ እስከ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን፤ የዓለም አገራት ስለ ኢንተርኔት አስተዳደር የሚመክሩበት፣ ለፓሊሲ አውጪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች የሚቀርቡ ምክረ -ሀሳቦች የሚነሱበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።