አገር አቀፍ የሰላም ምክር ቤት ተመሰረተ

98

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ አገር አቀፍ የሰላም ምክር ቤት ዛሬ በአዲስ አበባ ተመስርቷል።

በምስረታ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂን ጨምሮ የተለያዩ የጸጥታና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ምክር ቤቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሲሆን በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ሰላም ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመከወን ዕድል የሚፈጥር ነው።

"ሰላም የጋራ አጀንዳ፣ መንገድና መዳረሻ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ከሰላም ሁሉም አትራፊ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ልዩነቶችና አለመግባባቶች በውይይትና በሰከነ መንገድ የመፍታት ባህል እንዲዳብር ምክር ቤቱ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ለአገር ሰላም የሚተጉ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ተቋማቱ በምክር ቤቱ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ከሚረዱ መንገዶች አንዱ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሆኑን የተናገሩት አቶ ብናልፍ፤ የሰላም ምክር ቤቱ ኮሚሽኑ የሚሰራቸውን ተግባራት መደገፍ ላይ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት አለበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰላም ምክር ቤት ለመመስረት ባለፉት ሦስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

ምክር ቤቱ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ያቀፈ ነው።

ምክር ቤቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መሥራት እንዲሁም የግጭት አዝማሚያ ትንተናና መፍትሔ ማመንጨት ላይ እንደሚሰራ ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም