የሰላም ስምምነቱ ለውጤት እንዲበቃ የአማራ ክልል ምክር ቤት የበኩሉን ሚና ይወጣል - የክልሉ አፈ-ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ ለውጤት እንዲበቃ የአማራ ክልል ምክር ቤት የበኩሉን ሚና ይወጣል - የክልሉ አፈ-ጉባኤ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 የሰላም ስምምነቱ ለውጤት እንዲበቃ የአማራ ክልል ምክር ቤት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለፁ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፤ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ህዝቡ ከጦርነት ስጋት ወጥቶ በተረጋጋ መንገድ የታቀደውን ፈጣንና ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ እንዲተጋ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የሰላም ስምምነቱ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጥር በመሆኑ ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ የክልሉ ምክር ቤት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ስምምነቱ በመስኖና መኸር ልማት በስንዴ፣ በአኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች እየተመዘገበ ያለውን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
የግብርናው ምርታማነት ማደግ ክልሉ ካለው የማዕድንና ቱሪዝም እምቅ ሃብት ጋር ተዳምሮ የኢንዱስትሪ ልማትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተው የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረው ምክር የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ስራዎችን በመከታተልና በመቆጣጠር የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬና ነገ በሚያደርገው ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች በመምከርና ሹመቶችን በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።