የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በልማት ድል ማድርግ ይጠበቅበታል…የብአዴን ሊቀመንበር

145
መስከረም 17/2011 የአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ድህነትን ከልብ መጠየፍና በልማት ድል ማድረግ መሆኑን የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡ በብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በባህርዳር ከተማ መከሄድ ጀምሯል፡፡ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በቁጭትና እልህ  ሀገሪቱን  ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ  ትግል በመጀመሩ ተስፋ  ማየት በመታየት  ላይ ነው ብለዋል። ይህ ለውጥ የጎደለው የሚሞላበት፣ ያረጀው የሚታደስበት  የተጀመረው  ለውጥ ዳር የሚደርስበት  ስር ነቀል ጉዞ  መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ እያንዳንዱ ወቅትና ዘመን አርበኝነትን ይጠይቃል ያሉት ሊቀመንበሩ ለዚህ ትውልድ የ“አርበኝነት” ብያኔ ድህነትን ከልብ መጠየፍ እና በልማት ድል መንሳት መሆኑንም  አስረድተዋል። አቶ ደመቀ እንዳሉት  "ብዙ ውጣ ውረዶችን ተሻግረን የምናካሂደው ይህ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የመጣንበትን መንገድ በጥልቀት በማስተዋል የምንማርበት፤ ቀጣዩን ጎዳና በግልፅ የምናመላክትበት ሊሆን ይግባል፡፡" ብአዴን ለአማራ ህዝብና ለመድረኩ የሚመጥን ቁመና ተላብሶ ለውጡን ለማስቀጠል በየደረጃው በአዳዲስ ትውልድ የተገነባ አመራር መያዝ እንደሚጠይቀውና  ጉባኤው ከዚህ አኳያ ሃላፊነት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። "አዲሱ አስተሳሰብ  እንዲያሸንፍ፤ ለውጡም ህዝባችን የሚፈልገውን ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነትን እንዲያረጋግጥ ከተፈለገ መወጋገዙን ትተን መተጋገዝ፣ መጠላለፉን ትተን መተቃቀፍ፣ መሰባበሩን ትተን መተባበር መጀመር አለብን" ነው ያሉት የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ። የብአዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው አስተማማኝ የስራ እድል መፍጠር የወቅቱ የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ብአዴን ካሳለፋቸው የትግል እና የመምራት አመታት ልምድን በመያዝ በአዲሱ ዘመን ለውጥን በትክክለኛው አቅጣጫ ለመዘወር ትክክልኛ አቋም ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ አቶ ገዱ በመልእክታቸው "እንለወጥ ስንል ምክንያት አለን ክልላችን ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን የተመቸ አዲስ ተስፋ እንዲጎናፀፍ ነው " ብለዋል፡፡ የተገኘውን እድል በሚገባው መጠቀም  እንደሚገባም  አስታውቀዋል፡፡ የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ እንቅስቃሴው መሰረት እንዲይዝ ስርዓቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲመራ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች በየአካባቢው ለውጡን በባለቤትነት የመጠበቅ ስራን  በአንድነት፣ በሀሳብ የበለያንትና  በፍቅር እንዲጠብቁ  አስታውቀው፤ የተወሳሰበውን ችግር በአጭር ጊዜ መፍታት የሚቻለው በፍቅር እና በስራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም