የማላዊ የኢንፎርሜሽንና ዲጂታላይዜሽን ሚኒስትር ጎስፔል ካዛኮ አዲስ አበባ ገቡ

341

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2015 የማላዊ የኢንፎርሜሽንና ዲጂታላይዜሽን ሚኒስትር ጎስፔል ካዛኮ በ17ኛው የዓለም አቀፍ በይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ ከተማ ገብተዋል።

ሚኒስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ኢትዮጵያ 17ኛውን ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ እንግዶቿን በመቀበል ላይ ትገኛለች።

በጉባኤው ለመሳተፍም እስካሁን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገራት የተውጣጡ ከሦስት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ሲሆን ተሳታፊዎቹም ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንሁዋ ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።