ከማዕከሉ ያገኘነው የስንዴ ምርጥ ዘር ምርታማነታችንን እንድናሳድግ እየረዳን ነው-አርሶ አደሮች

307

ህዳር 18ቀን 2015 (ኢዜአ) ”ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኘነው የተሻሻለ የስንዴ ምርጥ ዘር ምርታማነታችን እንድናሳድግ እየረዳን ነው” ሲሉ በባሌ ዞን የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን የስንዴ ምርጥ ዘር በማሳቸው ላይ እያባዙ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳ በባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል።

የሲናና የግብርና ምርምር ማዕከል ለምግብነትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ በሽታን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ከአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሀሰን አብደላ በሰጡት አስተያየት ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን የተሻለ የሰብል ዝርያ ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ከዚህ በፊት ከአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን 30 ኩንታል ስንዴ ወደ 60 ማሳደግ መቻላቸውን ገልፀው ከምርት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ህይወታችንን እየለወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው አርሶ አደር ገመቹ ረጋሳም እንዲሁ ምርጥ ዘር በማይጠቀሙበት ወቅት በሄክታር ከ20 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር ገልጸው ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ግን በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ሚደቅሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በምርምር እየደገፈ ነው።

በተለይ በሰብል ልማትና በእንስሳት መኖ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ በማዕከሉ በምርምር የተለቀቁ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ ከ180 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በማዕከሉና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እየተባዙ ከሚገኙ የስንዴ የሰብል ዝርያዎች መካከል በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ‘ሃጫሉ’ና ‘ደምበል’ የሚል ሲያሜ የተሰጣቸው የስንዴ ዝሪያዎች ይገኙበታል።

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ቦጋለ በበኩላቸው የግብርና ምርምር ማዕከላት በምርምር የተገኙ የተሻለ ምርት የሚያስገኙ የሰብል ዝርያዎችን ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የሲናና ግብርና ምርምርን ጨምሮ በክልሉ ስር የሚገኙ 17 ማዕከላት ከዚህ በፊት የተለቀቁ ከ126 የሚበልጡ ዝርያዎች በአርሶ አደሩና በዘር አባዥ ማህበራት እየተባዙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

አቶ ተሾመ እንዳሉት የምርምር ማዕከላት በተለይ መንግስት የበጋ መሰኖ የስንዴ ልማትና ወደ ውጭ አገር ለመላክ የተያዘው ግብ እንዲሳካ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ናቸው።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጫላ አበበ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ከምርምር ማዕከላት የተገኙ ዝርያዎች በሰፊው ተባዝተው አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርስ በ17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተባዛ መሆኑን ተናግረዋል።

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል እስከ ከሁን 93 የሚሆኑ የሰብልና የእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ ለተጠቃሚው ማሰራጨቱ ተገልጿል።