የተፈጥሮ ሃብቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ ይገባል

153

ሰመራ ህዳር 18/2015(ኢዜአ)..የተፈጥሮ ሃብቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ።

በአፋር ክልል የተራቆቱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ የሚረዳ ክልላዊ ረቂቅ እስትራቴጂ እቅድ ዙሪያ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተካሄዷል

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም ባህል ባለመዳበሩ በሀብቶቻችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ነው።

ይህም ከአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ጋር ተደማምሮ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገዉ ገልጸው፤ መንግስት አደጋውን ለመቀልበስ የአረንጓዴ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ አያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ረቂቅ ስትራቴጂም ከአገራዊ ስትራቴጂው ጋር በተናበበ መልኩ በክልሉ ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ተደርጎ  መዘጋጀቱ ችግሩን በእግባቡ ለይቶ የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ አግባብ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚረዳ ነው ብለዋል።

በረቂቅ ስትራቴጂው ቀረጻ ሂደት የክልሉ መንግሰት ያሳየዉ ንቁ ተሳትፎና እገዛ በቀጣይም ሰነዱን በተሟላ አግባብ ወደተግባር ለመለወጥ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ርእሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማሻሻል ከሚሰሩ ሰፊ ጥረቶች መካከል አርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉትን የውሃ አማራጮች በአግባቡ መጠቀም ነው ብለዋል።


ይህም በአካባቢዎቹ የሚገኘዉን የእንስሳት ሀብት ለማሳደግ ከሚሰሩ ስራዎች ጋር ተመጋጋቢ ሆነው አጠቃላይ የግብርና ሴክተሩን ምርታማነት በማረጋገጥ በምግብ እራስን ከመቻል ባለፈ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለማዋል ማስቻል ነው ብለዋል።

ዛሬ ውይይት የተደረገበት ረቂቅ ስትራቴጂም ለዚህ ፈተና አየደቀነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተራቆቱ መሬቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲያገግሙ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረዉ ገልጸዋል።


ለተግባራዊነቱም የክልሉ መንግስት ህዝቡን ባሳተፈ አግባብ በትኩረት እንደሚሰራ ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተነሱ ነጥቦችን ግብዓት በማድረግ ስትራቴጂው ከቀጣዩ ዓመት አንስቶ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር በመድረኩ ተገልጿል።




የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም