የኢሬቻ በአል ወንድማማችነትንና አንድነትን ማጠናከሪያ ነው - የበዓሉ ታዳሚዎች

109

መቱ ኅዳር 18/2015 (ኢዜአ) --ኢሬቻ የወንድማማችነት፣ የአንድነት ማሳያና ማጠናከሪያ በዓል ነው ሲሉ የመልካ ሶር ኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።

በኢሉባቦር ዞን በየዓመቱ ኅዳር አጋማሽ ላይ የሚከበረው 'መልካ ሶር ኢሬቻ' በዓል ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ ታዳሚዎች በተጨማሪ ከጋምቤላና ከደቡብ ክልል አጎራባች ዞኖች የመጡ በበዓሉ ላይ ታድመዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ኢሬቻ የአንድነትና ወንድማማችነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ትልቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አባ ገዳ ተሰማ ሙሉነህ ኢሬቻ የወንድማማችነትና የአንድነት ማሳያና ማጠናከሪያ ነው ብለዋል።

''የኢሬቻን በዓል ስናከብር ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር አብሮነታችንን በሚያጠናክር ሁኔታ በመሆኑ በዓሉ ልዩ ገጽታ አለው'' ብለዋል።

በተጨማሪም የኢሬቻ በዓል አብሮነት የሚጠናከርበት ዕለት እንደሆነም ተናግርዋል።

በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ  ከጋምቤላ ክልል አቶ ፒተር ሆ ፣የኢሬቻ በዓል ሕዝቦችን የበለጠ የሚያቀራርብ መሆኑን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በብዙ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሰፋፊ መስተጋብሮች ያሉት መሆኑንም ጠቁመዋል።

''የኢሬቻን በዓል በአብሮነት ስናከብር ሌሎች አብሮነታችንን የሚያጠናክሩ መንገዶች ይከፈታሉ'' ሲሉም አክለዋል።  

በበዓሉ ላይ የውጪ አገር ዜጎችም የታደሙ ሲሆን ኢሬቻ ሕዝቦች በብዛት ሆነው በአንድነት የሚያከብሩት መሆኑን መታዘባቸውንና በበዓሉ ላይ በመታደማቸውም መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም