ታላቅ ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያስፈልገናል – የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች

236

አሶሳ ህዳር 18/2015(ኢዜአ) “ታላቅ ሀገር የሆነቸውን ኢትዮጵያ ለማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያስፈልጋናል” ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከልል 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማጠቃለያ መርሐግብር ዛሬ በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

በቀኑ አከባበር ላይ ከተሳተፉት የከተማው ነዋሪዎች “ህብረ ብሄራዊነት ለዘመናት የቆየ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው”፤ይህም ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን አስጠብቋል ብለዋል።

ጠንካራ ባህላዊ እሴቶቻችንን ከማልማት ባለፈ ለትውልድ ጠብቆ ማስተላለፍ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከድህነት የምንላቀቀው ደግሞ ሕብረ ብሔራዊ አንድታችንን በማስጠበቅና ሰላማችንን ማስቀጠል ሲቻል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ እንደ ሀገር ለመቀጠል ጠንካራ አንድነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋሂድ  በክልሉ የመጣውን ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው የሕብረተሰቡ ድጋፍ እና ርብርብ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ በበኩላቸው አሁን የጀመርነውን ሰላምና የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት መውጣት እንችላለን ብለዋል፡፡

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን  “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ሀሳብ  ሕዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሃገር አቀፍ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ ይከበራል።