መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበላቸው መሆኑን የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

99

ሰቆጣ ኢዜአ ህዳር 18/2015 ዓ/ም ...መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበላቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተደረሰው የሰላም ስምምነት አንዱ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍን ፈጥኖ ማድረስ ነው።

ከከተማ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ እስከዳር ኃይሌ ከአንድ ዓመት በላይ የኮረም ከተማ ህዝብ  በችግርና ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ ህይወቱን መርቷል ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዋ አያይዘውም   በኮረም ከተማና አካባቢው አሁን ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ ከተማዋ ወደ ቀደሞ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ገልፀዋል።

በመንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ጊዜ ጀምሮ መንግሥት የምግብ እህል ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ የህዝቡን ችግር አቃሏል ብለዋል።


ቄስ ሃጎስ አራርሶ በበኩላቸው ባጋጠመው ችግር ምክንያት የኮረምና አካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ የሰብዓዊ ችግር ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል።


በከተማዋና አካባቢዋ አሁን በሰፈነው ሰላም ህዝቡ ወደ ቀደመ ህይወቱ መመለሱን ጠቅሰው፤ በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት የህዝቡን ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።


መንግሥት አስቸኳይ የምግብ እህል እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የምግብ እህል እርዳታ ድጋፍ ማድረጉ የህዝቡን ስር የሰደደን ችግር ያቃለለ መሆኑንም አስረድተዋል።


በመንግሥትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው ስምምነት ተግባራዊነት ሁሉም ወገን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


ወጣት መለሰ አደሩ በበኩሉ በፌዴራል መንግሥትና ህውሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት በኮረም ከተማ የገበያና የንግድ ተቋማት ወደ ቀደሞ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል ብሏል።


አጋጥሞ በነበረው ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጿል።

መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በፍጥነት ተደራሽ ማድረጉ ህዝቡ የነበረበት መሰረታዊ ችግር መቃለሉንም ወጣት መለሰ አስረድቷል።


በባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው ችግር ምክንያት በርካታ ዜጎች ለሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መዳረጋቸውን የኮረም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘማቹ በላይ አስታውሰዋል።


በኮረም ከተማና አካባቢው በጦርነቱ ምክንያት የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ውድመት የደረሰ ቢሆንም ከሰላም ስምምነቱ ማግሥት ጀምሮ መንግሥት መልሶ የማቋቋም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።


ከንቲባው አያይዘውም እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች የስልክ ፣መብራትና ውሃ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ጠቅሰው፤  የጤና ተቋማትና የመንግሥት አገልግሎቶች የመመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


ከዚህ ጎን ለጎንም አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እየቀረበ መሆኑን  ተናግረዋል።


መንግሥት የሰላም ስምምነቱን  ለመተግበር በገባው ቃል መሰረት በፍጥነት የምግብ እህል በማቅረቡ ህዝቡ  ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ ማስቻሉንም አስረድተዋል።


የኮረም ከተማ ወደ ቀደመ እንቅስቃሴዋ አየተመለሰች መሆኗን የተናገሩት ከንቲባው በኮረም አለማጣና ሰቆጣ ከተሞች የህዝብ ትራንስፓርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።


በቀጣይም የባንክ አገልግሎት ጨምሮ ሌሎች በጦርነቱ የወደሙ የጤናና ትምህርት ተቋማት መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም