''የሌማት ትሩፋት'' መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን በላቀ ቅንጅት መስራት ይገባል --- አቶ ታገሰ ጫፎ

144

ቻግኒ ህዳር 18/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሟላትና የዜጎችን የአመጋገብ ስርዓት በመለወጥ ''የሌማት ትሩፋት'' ውጤታማ እንዲሆን በላቀ ቅንጅት መስራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ።

በአማራ ክልል ''የሌማት ትሩፋት'' ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ታገሰ ኢትዮጵያ በሁሉም የተፈጥሮ ሃብት የታደለች መሆኗን ገልጸው ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ መልክዓ ምድር፣ ተስማሚ የአየር ፀባይ፣ በርካታ የእንስሳት ሀብትና እምቅ የውሃ ሀብት የእድገት ጸጋዎቿ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ታገሰ አያይዘውም ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚቻልበት እድል ሰፊ መኖሩንም አመላክተዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር እያንዳንዱ ቤተሰብ የተትረፈረፈ ምርት በጥራትና በመጠን አምርቶ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ ማድረግ የሚያስችል ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

“ለዚህም በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ በመለየት መስራትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ሲሉ” አስገንዝበዋል።

አርሶ አደሩ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ በየደረጃው ያለው አመራርም ሆነ የግብርና ባለሙያ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀደለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የሌማት ትሩፋትን ግብ ለማሳካት የሚያስችል አቅም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል መኖሩን የገለፁት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።

አርሶ አደሩን ማንቃትና ማስተባባር ከተቻለ በጥራትም ሆነ በመጠን የተትረፈረፈ ምግብ በማምረት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ይቻላል ብለዋል።

ለዚህ ደግም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለስንዴ ምርት የተሰጠው ትኩረትና እየተገኘ ያለው ውጤት ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ የሚገኙ ምርቶችን ትኩረት ሰጥቶ በማምረት በተመጣጠነ ምግብ እጦት ምክንያት የሚከሰትን የመቀንጨር በሽታ ማስወገድ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራርና የግብርና ባለሙያ በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ባለው መርሃ-ግብር የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የፓናል ውይይት፣ የእንስሳት ሃብት ጉብኝትና መሰል ፕሮግራሞች ተካታውበታል።

የሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በይፋ ማስጀመረቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም