በመዲናዋ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የችግኝ እንክብካቤ ስራ ተከናወነ

188

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ህዳር 18/2015 በአዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፉን የበጎ ፈቃድ ሳምንት ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት የችግኝ እንክብካቤ ስራ ተከናወነ፡፡

ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ሳምንት "በጎ ፈቃደኝነት ለማህበራዊ መስተጋብር" በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከበረ ይገኛል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስተባባሪነት በከተማ ደረጃ 24 ሺህ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት የችግኝ እንክብካቤ ስራ ተከናውኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ዓለም አቀፉ የበጎ ፈቃድ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ችግኞችን ከመንከባከብ ባሻገር የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስ፣ ማዕድ የማጋራት እና ደም የመለገስ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞች በበኩላቸው ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በበጎ ፈቃድ የመንከባከብ ባህል ሊዳብር ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ቀጣይነት ባለው መልኩ ችግኝ የመንከባከብ ስራ ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡

በክረምት ወቅት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ተግባር በበጋውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡

በመዲናዋ በበጋ በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከ246 ሺህ 850 በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ  ከ353 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ መገለጹ ይታወሳል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ 2 ቢሊዮን ብር የመንግስት ወጪን ለማዳን መታቀዱን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም