የአማራ ክልል ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ ይጀመራል

151

ባህርዳር ኢዜአ ህዳር 18 ቀን 2015 የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነገ ማካሄድ እንደሚጀምር የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ።

አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ ከህዳር 19-20/2015 ዓ.ም ለ2 ቀናት በሚያደርገው ቆይታ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

ቀደም ሲልም ክልሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የምክር ቤት አባላት ወደ ተመረጡበት አካባቢ በመሄድ ህዝቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ ባከናወኑት የማነቃቃት ስራ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ስራ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተማሪዎች ትምህርት አጀማመር፣ የአሚኮ የ2014 በጀትና የ2015 ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።

በተለይም በትምህርት ግብዓት አቅርቦትና በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ስነ-ምግባር የታነፁ ሆነው እንዲያድጉ ምክር ቤቱ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ያስቀምጣል ሲሉ ገልፀዋል።

እንዲሁም የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ግኝት ሪፖርት አፈፃፀም ቀርቦ ምክር ቤቱ በኦዲት ግኝት አመላለስ ዙሪያም በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ የተገኘው ሰላም ዘላቂ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ አተኩሮ የሚወያይ ሲሆን በመጨረሻም ልዩ ልዩ ሹመቶችን በመስጠትና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ጉባኤውን ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም