የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ለሶማሌ ክልል 400 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ለሚካሄዱ የግብርና ስራዎች የሚያግዝ 400 የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን በድጋፍ አበረከተ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ድጋፉን ለሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት ኢንጂነር አይሻ ባደረጉት ንግግር የሌማት ትሩፋት በተለይ ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ፕሮጀክት በመሆኑ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ርብርብ ማሳካት ይኖርብናል ብለዋል።

የፓፕሞቹ ድጋፍም የክልሉን አርብቶ አደር የግብርና ስራዎች በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።

ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ በበኩላቸው የሌማት ትሩፋትን ለማሳካት ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል በማለት ክልሉ ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሀብት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም