የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በሀገሪቱ የትምህርት ዘርፍ የድርሻውን አበርክቷል- የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

152

ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በሀገሪቱ የትምህርት ዘርፍ በመሳተፍ የድርሻውን ማበርከቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

በሐረር ከተማ የሚገኘው የሰዎች ለሰዎች የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ አክብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበጎ አድራጊው ዶክተር ካርል ሄንዝ በም የተመሰረተው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ላለፉት 40 ዓመታት በርካታ ሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ሲሰራ ቆይቷል።

ድርጅቱ በዘላቂ የመሬት ሀብት አጠቃቀም፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ፣ በሰው ሀብት ልማትና በትምህርት ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ድርጅቱ ባከናወናቸው ተግባራት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የገጠሩ ማህበረሰብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛልም ብለዋል።

ድርጅቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 463 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችና ሰባት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመገንባት ዜጎች የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ድርጅቱ በሐረር ከተማ ከ30 ዓመት በፊት በከፈተው የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ከሀገሪቱ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተማሪዎችን ተቀብሎና የትምህርት አገልግሎትን ጨምሮ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ በዲፕሎማና በድግሪ መርሃ ግብሮች እያሰለጠ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

“በአዲስ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ጽንሰ ሃሳብ” መሰረት ትምህርት ቤቶችን እንደ አዲስ መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በኢትዮዽያውያንና በትውልደ ኢትዮዽያውያን ዳያስፖራዎች፣ በትምህርት ልማት አጋር ድርጅቶች፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ተሳትፎና ድጋፍ ነው።

የሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅትም 16 ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ በገባው ቃል መሰረት ወደ ስራ መገባቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ካለፉት 40 ዓመታት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ትምህርት ቤቶቹን በአዲሱ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን መሰረት እንደሚያድስ፣ እንደሚያዘምንና እንደሚያስፋፋም ይጠበቃል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ድርጅቱ ሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳስበዋል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለግብርናው ዘርፍ ተስማሚ ቴክኖሎጂ በማፍራት ለምርታማነት ዕድገት የድርሻውን እያበረከተ ነው ያሉት ደግሞ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው።

ኮሌጁ የአርሶ አደሩን ህይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂን በማሸጋገርና የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትና በብቃት እያፈራ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ሀገሪቱ ለጀመረችው የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ስኬት መልካም ተሞክሮውን ለሌሎች ተቋማት በማካፈል የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የሰዎች ለሰዎች  የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ፕሬዝዳትን ዶክተር ጌታቸው ሹንኪ በበኩላቸው ኮሌጁ በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ኮሌጁ ለአካባቢው ማህበረሰብ በስልጠና፣ በልማት ዘርፎች የመደገፍና የማብቃት እንዲሁም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥና ራስን በመቻል ረገድ ተግቶ ይሰራልም ብለዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶክተር ሲሞኔ ክናፕ የተገኙ ሲሆን ድርጅቱ ለበርካታ ዜጎች የልማት ስራዎችን በማከናወን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኮሌጁ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰባስቲያን ብራንዲስን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የኮሌጁ የተግባር ማሰልጠኛ ማዕከላት ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም