በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማስተሳሰር እንደሚሰሩ ገለጹ

394

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማስተሳሰር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ በደቡብ ክልል የከምባታ ጠምባሮ፣ ወላይታና ጎፋ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች አመለከቱ።

ዋና አስተዳዳሪዎቹ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የስራ ዕድል ፈጠራን በማበረታታት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ያላቸውን የትኩረት አቅጣጫ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

በዞኖቹ ያለውን የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ዕምቅ አቅምና አመቺነት በመጠቀም ስራ አጥ ወጣቶችን በዘርፉ በማደራጀት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

የከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ አጭሶ፣ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤት ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ የበለጠ ይሰራል ብለዋል።

በወተት ላም እርባታ በተከናወኑ የዝርያ ማሻሻያ ስራ የወተት አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል ተስፋ መታየቱን ጠቁመዋል።

የወተት ምርታማነትን ከማሻሻል በተጓዳኝ የሚመረተውን ምርት አቀነባብሮ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል በክልሉ መንግስት በኩል የወተት ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ለስጋ የሚሆኑ እንስሳትን የማደለብ ስራ ከወተት ምርታማነት ማሳደግ እኩል ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቁመዋል።

በተለያዩ መስኮች ዜጎችን በማደራጀት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ መሰረት እንዲሰራ በማድረግ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የገለጹት የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች፤ ያለንን የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ዕምቅ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በተለይም በአሁኑ ሰዓት በገበያው ላይ ያለው የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መልኩ ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዳልጋ ከብት ብቻ ሳይሆን በዶሮ እርባታ የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦት ላይ በትኩረት በመስራት እያንዳንዱ አባወራና እማወራ በቤቱ የዶሮ እርባታ እንዲያከናውን የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ በአርባምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ይፋ 

የተደረገ ሲሆን በዋናነት አርሶ እና አርብቶ አደሩን እንዲሁም ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው።