የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ትውልዱ ባህልና ቋንቋውን አውቆና ጠብቆ እንዲጓዝ መነሳሳትን ይፈጥራል

193

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ትውልዱ ባህሉን፣ ቋንቋውንና አብሮነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ መነሳሳትን ይፈጥርለታል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልቃድር ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች ሲያካሂድ የቆየው የጥያቄና መልስ የማጠቃለያ ውድድር ተካሂዷል።

ቀኑን አስመልክቶ በተደረገው ጥያቄና መልስ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎችም የከተማ አስተዳደሩ ሽልማት አበርክቷል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልቃድር እንዳሉት፤ በዓሉ የሕዝቦች አንድነት እንዲጠናከርና ዜጎች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና እንዲያስተዋውቁ ያግዛል።

ትውልዱም በባህልና እሴቱ የሚኮራና ለነገው ትውልድም ጠብቆ እንዲያቆየው መነሳሳትን ከመፍጠር ባለፈ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ያግዛል ብለዋል።

ቀኑ በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል፤ ዛሬ የተካሄደው የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድርም አንዱ ነው ብለዋል።

የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤  የበዓሉ መከበር ተማሪዎች የአገራዊ አንድነትና ፍቅርን እንዲረዱ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥና ልማቱ እንዲፋጠን ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው የራሳቸውን አሻራ ለማኖር መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋልም ብለዋል።

የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ በፓናል ውይይት፣ በተለያዩ ፌስቲቫሎች፣ እንዲሁም በጥያቄና መልስ ውድድር ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።

በውድድሩ አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት ያሸነፉት ተማሪ ነጂባ አማን እና ፍቅር በሱፍቃድ ውድድሩ ስለ አገራችን ሕገ-መንግሥትና ሕዝቦች እንድናውቅና ግንዛቤ እንዲኖረን አግዞናል ብለዋል።

"ሽልማቱ በቀጣይ በትምህርታችንም ጠንክረን እንድንማር ትልቅ ሞራል ሰጥቶናል" ሲሉም ተናግረዋል።

ተሸላሚ ከሆኑ መምህራን መካከል ሲሳይ ተስፋዬ እና ገንዘቤ ገለታ የጥያቄና መልስ ውድድር መካሄዱ ስለ አገራቸው የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።

በተለይ በተማሪዎች መካከል አንድነትና መተሳሰብን በማጠናከር ጥሩ ዜጋን ለመፍጠር እንደሚረዳም አክለዋል።

በዕለቱ በተደረገው ውድድር ላሸነፉ ተማሪዎች አይፓድና ሞባይል ቀፎ የተሸለሙ ሲሆን፤ ለትምህርት ቤቶች ደግሞ ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።

የዘንድሮ 17ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሐዋሳ "ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም