በግብርናው ዘርፍ የታየው ምርታማነት የሃገራችን ለውጥ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ውስጥ ስለመሆኑ ማሳያ ነው--ዶክተር ይልቃል ከፋለ

164

ባህር ዳር ኢዜአ ህዳር 17/2015 ''በግብርናው ዘርፍ የታየው ምርታማነትና የታላላቅ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የተጀመረው የአገራችን ለውጥ በፈጣን የእድገት ምህዋር ላይ መግባቱን ማረጋገጫ ነው'' ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ-መስተዳድር ገለፁ።

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ ለባለሃብቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ፎረም በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።

ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በፎረሙ ላይ እንዳሉት የክልሉ መንግስት የገጠመውን የፀጥታ ችግር ከመቋቋም ጎን ለጎን ለልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ አድርጓል።

በዚህም መላ አርሶ አደሩንና ባለሃብቱን በማስተባበር በተካሄደው የመኽር ሰብል ልማት አሁን ላይ ከፍተኛ ምርት ማምርት እንደሚቻል ተረጋግጧል ብለዋል።

ይህም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ለጥሬ እቃ የሚሆን ምርት እጥረት አለ ሲባል የነርበርውን ምክንያት የሰበረ ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የሚመረተውን የስንዴ፣ የአኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች በግብአትነት የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ባለሃብቶች ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስትም የግብርናውን ምርት ከማሳደግ ጎን የጎን የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለአልሚ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

''በዚህ ፎረም የምትሳተፉ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብታችሁ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት አገራችን የጀመረችውን እድገት እንድታፋጥኑ'' ሲሉ አሳስበዋል።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የታየው የምርት እድገትና የታላላቅ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ በፈጣን የእድገት ምህዋር ውስጥ መግባቱን ማረጋገጫ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳደሩ አብራርተዋል።

የቡሬ ኢግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአስፓልት መንገድ፣ የውሃ፣ የቴሌ የአንድ ማእከልና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟላለት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው።

ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው በማልማት ራሳቸውን ጠቅመው የአገራቸውን እድገት እንዲያፋጥኑም ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስትም በፓርኩ ለማልማት ለሚመጡ ባለሃብቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በፎረሙ የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ ባለሃብቶች፣ ዩኔኖች፣ የህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም