በሰዎች ለሰዎች ደርጅት የተቋቋመው የሀረር አግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 30ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው

265

ሀረር (ኢዜአ ) ህዳር 17 ቀን 2015 በሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅት የተቋቋመው የሀረር አግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 30ኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ክብረ በዓሉ ለመታደም ሐረር ከተማ ገብተዋል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት እ ኤ አ በ1981 በዶክተር ካርል ሄንዝ በም በጀርመን ሙኒክ ከተማ ተመሰረተ፤ኋላም ድርጅቱ በኦስትሪያና በስዊዘርላንድ ተቋቁሞ ላለፉት 40 ዓመታት በአገራችን በሁሉም አቅጣጫ በልማቱ ዘርፍ እያገለገለ የሚገኝ አንጋፋ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

ድርጀቱ በተለይ በትምህርት ዘርፍ በሐረሪ ክልል የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅን በመክፈት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በርካታ ሰልጣኞችንና ተማሪዎችን በሰርተፍኬት፣በዲፕሎማና በመጀመሪያ ድግሪ አሰልጥኖ አስመርቋል።

በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የአግሮ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋንና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል ባለስልጣናት እና የድርጅቱ አመራሮች ሐረር ከተማ በሚገኘው ኮሌጅ ተገኝተዋል።

በክብረ በዓሉ ኮሌጁ የ30 ዓመት የትምህርት አሰጣጥ እና የመማር ማስተማር ሂደት ገለጻ ይቀርባል።

እንዲሁም በኮሌጁ ተማሪዎች የተከናወኑ የቴክኖሎጂ ስራዎች ለእይታ ቀርበው ይጎበኛሉ።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የተመሰረተበት 40ኛ ዓመቱ ክብረ በዓል በተያዘው ዓመት በአዲስ አበባ፣ጀርመንና ኦስትሪያ መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም