ቀጥታ፡

ከሁመራ -ሽራሮ እስከ ሽሬ ድረስ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ከ20 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

ህዳር 16/2015 (ኢዜአ) ከሁመራ -ሽራሮ እስከ ሽሬ ድረስ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ከ20 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

የአካባቢው ነዋሪዎች  አገልግሎቱን በፍጥነት ለማስቀጠል እየተከናወነ ባለው ስራ ላይ እያደረጉት ላለው ድጋፍም ተቋሙ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት በአካባቢዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም አካባቢዎቹ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ እየተሰራ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ክፍል ቴክኒካል ድጋፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሰሜን ምስራቅና ሰሜን ምዕራብ ሪጅን የሚያስተዳድራቸው ከፍተኛ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማከፋፈያዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ቆይቷል፡፡

በወቅቱ ከተከዜ እስከ አድዋ ያለው ጥገና ተደርጎለት ኃይል ማስተላለፍ ቢጀምርም በጦርነቱ ምክንያት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም  ጉዳት ማስተናገዱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በመልሶ ግንባታ 474 ታወር ያለውና 260 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ከሁመራ -ሽራሮ እስከ ሽሬ ጉዳት የደረሰባቸው የኃይል አስተላላፊ መስመሮች ጥገና ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው 92 የሚሆኑ የኃይል ማስተላለፊያና ሌሎች የኃይል የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች ውስጥ 68ቱ ተጠግነው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ቀሪዎቹ ስራዎች በሚቀጥሉት አራት ቀናት ተጠናቀው፣ ወደ አክሱምና አድዋ መስመሮች ጥገና እንሸጋገራለን ብለዋል።

የሁመራ- ሽራሮ- ሽሬ የኃይል አስተላላፊ መስመሮችና ማከፋፈያዎች ጥገና ከተጠናቀቀ በኋላ ቀሪው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ መሆኑን በፍተሻ አረጋግጠናል ብለዋል።

በመሆኑም የኤሌክትሪክ ሀይል አስተላላፊ መስመሮችና ማከፋፈያዎች ጥገና ተጠናቆ ከ20 ቀን ባጠረ ጊዜ ሁሉም አካባቢዎች መብራት ያገኛሉ ብለዋል።

በኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደመድረሱ መጠን የግብዓት ዕጥረት ቢያጋጥምም ህብረተሰቡ በኃይል እጦት የደረሰበትን ችግር ታሳቢ በማድረግ ቀን ከሌሊት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች  ስራቸው በፍጥነት እንዲያከናውኑ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም