የሰውን ሀብት ባልተገባ መንገድ ማግኘትም ሆነ ለማግኘት መሞከር የተወገዘ ነው- የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች

274

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ህዳር 16 / 2015 የሰውን ሀብት ባልተገባ መንገድ ማግኘትም ሆነ ለማግኘት መሞከር የተወገዘ መሆኑን  የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሙስና ድርጊት ለመከላከል መንግስት የጀመረውን ዘመቻ አስመልክቶ ኢዜአ ከጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ የሙስና ድርጊት በየትኛውም ማህበረሰብ ዘንድ ነውር መሆኑን ገልጸው፤ በህግም በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን አመልክተዋል።

“ሰው በላቡ ያላመጣው ሀብት በረከት የለውም” ያሉት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች፤ የደሃዉን ህዝብ ሀብት ባልተገባ መንገድ የሚነጥቁ ሁሉ ለቤተሰቦቻቸው መከራን እንጂ ሀብትን ሊያወርሱ አይችሉም ብለዋል።

የጋሞ አባቶች እንደሚሉት፤ የሰውን ሀብት ባልተገባ መንገድ ማግኘትም ሆነ ለማግኘት መሞከር የተወገዘ ነው።

ለኢዜአ አስተያየታቸዉን የሰጡት የጋሞ አባት አቶ ተፈራ ኦይቻ እና ካዎ ኤልዶ ኤማኔ ከጋሞ ባህል አንፃር ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል “ጎሜ” ወይም ሃጢያት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ሀጢያት መከራ የሚያስከትለው የሙስና ድርጊት በፈጸመው ግለሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጆቹም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ህዝቡ የራሱ ያልሆነን በተለያየ ምክንያት አስገድዶ መቀበል ይቅርና ወድቆ ያገኘውን እንኳን ለመንግስት ያስረክብ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ዜጎች መብታቸውን ለማግኘት በገንዘብ እንዲገዙ መገደዱ በአገሪቱ የወደፊት እድገት ላይ እንቅፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሰው የላቡን ብቻ እንዲያገኝ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉም አካል ሙስናን ለመከላከል መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሙስናን ለመከላከል መንግስት የጀመረውን ዘመቻ ያደነቁት የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎቹ አቶ ተፈራ ኦይቻ እና ካዎ ኤልዶ ኤማኔ፤ በዚህ ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በሙስና ሀብት የሰበሰቡ ሰዎች ሰርቀዉና ዘርፈዉ በመሆኑ የአዕምሮ ሰላምና እርካታ የሌላቸዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በሙስና ህንፃ ከመገንባት ይልቅ በንጹህ ህሊና ጎጆ ቤት ዉስጥ መኖሩ ይሻላል ነዉ ያሉት ።

በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሙሰኞችን በማጋለጥ ረገድ ማህበረሰቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደምገባ አመልክተው፤ ከህጻናት ጀምሮ የሙስናን አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ በመፍጠር የተጀመረውን ትግል ስኬታማ ለማድረግ በስርዓተ ትምህርት ጭምር በማስገባትና በሀይማኖት ተቋማትና በቤተሰብ ደረጃ ለልጆች በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ የሀገር ሽማግሌዎቹ አመልክተዋል።

መንግስትም የሙስና ድርጊት ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ህዳር 08 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል።