በዓሉን ስናከብር የተገኘውን ሰላም ለማጽናት ቃላችንን በማደስ ነው- የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ

154

ዲላ  (ኢዜአ) ህዳር 16 / 2015  የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ስናከበር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ሥር እንዲሰድና የተገኘውን ሰላም በይበልጥ ለማጽናት ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባለ ሲሉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ አስገነዘቡ ።

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን“ በሚል መሪ ቃል በዲላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ የተገኙት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ እንዳሉት በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ አንድነታቸውን የሚያሳዩበት ነው።

በተለይ በደቡብ ክልል የተለያዩ ማንነቶች ህገ መንግሥታዊ እውቅና ከማግኘታቸው ባለፈ ውብ ባህሎችና እሴቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ፀጋዎች የሚተዋወቁበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህም ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብትና በፅኑ መሰረት ላይ እንድንቆም ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉን ስናከብር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ከማጠናከር በተጓዳኝ የተገኘውን ስላም ለማጽናት ቃላችንን በማደስ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ወይዘሮ ፋጤ አክለውም በተለይ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማጎላት እጅ ለእጅ ተያይዘን በህብረት መስራት ይገባል ሲሉም በአጽዕኖት ገልጸዋል።

በዓሉ በሁሉም አካባቢዎች በጎ ተግባራትን በማከናወን፣ በህገ መንግሥቱ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር አንድነታችንን እና አብሮነታችንን በሚያጠናክር መንገድ  እየተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓሉ ሀገራችን ወደ ሰላም በመጣችበት በተለይ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በተገኘበት ማግሥት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ ናቸው።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት በዓሉ በብሔር ብሔረሰቦች ትግል የተረጋገጠውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ከማጠናከር ጎን ለጎን የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና በጥረታችን ለማረጋገጥ የምንነሳሳበት ነው።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ትበቃለች ያሉት አቶ አብዮት ለሀገራችን ለዘላቂ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና እንስራ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ የሥራ ኃላፊዎች፣አባ ገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎችና የዲላ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች አልባሳትና እሴቶች በማስተዋወቅ በስፖርታዊ ውድድሮች እንዲሁም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም