በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ሁሉም በጽኑ ሊያወግዘው ይገባል- ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

151

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም አመለካከቱንና ድርጊቱን በጽኑ ሊያወግዘው እንደሚገባ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ የዘንድሮውን የ16ቱን ቀናት የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ በይፋ አስጀምረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያደነቁት ፕሬዚዳንቷ፤ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ሴቶችና ህጻናት ፍትህ እንዲያገኙ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 01 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት 16 ቀናት የሚከናወኑ የዘመቻ ስራዎች ላይ የፓናል ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የጸረ- ጾታዊ ጥቃት  ቀን በተደጋጋሚ  የሚፈጸሙ ጾታዊ  ጥቃቶችን  መከላከል  ላይ ትኩረት አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄድ ዘመቻ ነው።

ከህዳር 16 ቀን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 01 ድረስ በየዓመቱ በሚካሄድ በ16 የንቅናቄ ቀናት በፆታዊ ጥቃት ምክንያት የሚከሰቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች በተመለከተ ግንዛቤ የማስጨበጥና ችግሩን በዘላቂነት መከላከል የሚቻልባቸው ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት በስፋት የሚሰራበት ወቅት ነው።

በተለይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትና ኅብረተሰቡ በአካባቢያቸው ለሚገኙ ሴቶች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰብን ይጨምራል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም