የሌማት ትሩፋት - የሀገርን መሶብ በምግብ የመሙላት ውጥን

1501

አለቃ ደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላታቸው የሌማትን አንድምታ ከመዓድ ማስቀመጫና ማቅረቢያነቱ፣ ከመሶብነቱ ባሻገር ከሕብስት መትረፍረፍና ከሲሳይ ሙላት ጋር ያቆራኙታል።

ሌማት በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የተቸረው፣ በስነ-ቃል እና ይትባህሃሉ የታጀበ አንድምታም አለው።

አበው ሲመርቁ "መሶብ አይጓደል"፣ "በእንጀራ ይሙላ ሌማቱ፤ ወጡም በየአይነቱ" እንዲሉ፤ እናት በአገር ትመሰላለችና በሌላ አነጋገር አገር መሶቧ እንዳይጎድል፣ ሌማቷ በሲሳይ እንዲትረፈረፍ መመኘት ነው።

መንግስትም ለዚህ ይመስላል 'አገር ከኩርማን እንጀራ፣ ከጠኔ አዙሪት' ትፋታ ዘንድ በቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር "የሌማት ትሩፋት" መርሃ ግብርን በቅርቡ ያበሰረው።

የ'ሌማት ትሩፋት' የአገርን ጓዳ 'በእንስሳት፣ በዶሮ እና በማር' ምርቶች በማትረፍረፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘውን ስኬት መድገም ነው።

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው 'የሌማት ትሩፋት' መርሐ-ግብር በምግብ ሉዓላዊነት ማስከበር እና ክብርን ከማረጋገጥ ጋር ቁርኝት አለው።

የ'ሌማት ትሩፋት' መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ ማስቻል፤ በተለይም በስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ቅንጦት ሳይሆን ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን በቅጡ ካለማች የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የቅንጦት ምግቦች ሳይሆኑ ከሌማት ከማይለዩ፣ በዕለታዊ ምግቦች ማባያነት የማይታጡ ግብዓቶች ማድረግ እንደሚቻል እሙን ነው።

ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት አመርቂ ውጤት ሳያገኝ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ዘርፉ በቅንጅት ከተመራ፣ በቴክኖሎጂ ከታገዘ አማራጭ የምግብ ግብዓቶችን ማብዛት ይቻላል።

ወተት፣ ማር፣ ስጋ እና እንቁላል መሰል የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በገበያ ላይ በቀላሉ ማትረፍረፍ፣ የሌማቱ በረከት ማብዛት የሚለው የብዙሃኑ እምነት ነው።

የ"ሌማት ትሩፋት" መርሐ-ግብር የእንስሳት ተዋእፆ ምርት እምርታን ማረጋገጥ እና ከእምርታው ፍሬም የመቋደስ ግብ ሰንቋል።

ለእንስሳት የሚስማማ አየር፣ ለንቦች አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር፣ ስጋ እና እንቁላል ሊያትረፈርፍ የሚችል ተፈጥሮም ያላት አገር ናት ኢትዮጵያ! ይህንን አቅም ከመጠቀም አንጻር ግን አሁንም ብዙ ርቀቶች ይቀራሉ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር ሲሆን ዓመታዊ የወተት የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ደግሞ ከ66 ሊትር እንደማይበልጥ ነው የሚገለጸው፡፡

ይህም ለአንድ ጤነኛ ሰው በዓመት ከሚያስፈልገው 200 ሊትር አንጻር በእጅጉ ያነሰ መጠን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የተቀነባበሩ የወተት ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ በአማካኝ ከ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ መረጃው ይጠቁማል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በአማካኝ በዓመት 40 እንቁላል ብቻ የሚጥሉ ሲሆን፤ በተለያዩ አገራት ግን በዘመናዊ የዶሮ እርባታ አማካኝነት በዓመት ከአንድ ዶሮ 270 እንቁላል ማምረት መቻሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው በዚሁ መርሃ-ግብር ዓመታዊ የወተት ምርትን አሁን ካለበት 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሊትር ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር የማድረስ ግብ መያዙም እንዲሁ፡፡

በተጨማሪም የዶሮ ስጋ ዓመታዊ ምርትን አሁን ካላበት 90 ሺህ ወደ 240 ሺህ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ቶን ከፍ ለማድረግ ይሰራል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአርባ ምንጭ ተገኝተው መርሃ ግብሩን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የዜጎችን የምግብ መሶብ ከማሳ ጋር የሚያስተሳስር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ቤተሰብን ከመመገብ ባሻገር በምግብ ራሷን የቻለች አገር የሚገነባበት መንገድ መሆኑም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ አረንጓዴ አሻራና ሌሎች በርካታ አገራዊ የልማት እቅዶችን እውን እያደረጉ ነው፡፡

ይህንኑ ስኬታማ ጉዞ በሌማት መርሃ-ግብር መድገም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም መርሃ-ግብሩ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን የከተማውን ህብረተሰብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል፡፡

በዚህም መርሃ-ግብሩ በልቶ ከማደር በላይ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ ታሪካችንን ይቀይራል ነው ያሉት፡፡  

መርሃ-ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ መንግስት ዝርዝር ጥናት አድርጎና ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በዋናነት አራት ዓላማዎችን እንደያዘ ይናገራሉ፡፡

ከዚህም ውስጥ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ስርዓተ ምግብን ማሻሻል እንደዋነኛ ዓላማ ተይዟል፡፡

በሂደቱም በከተማና በገጠር ለሚኖሩ በርካታ ዜጎች በምርት እና ገበያ ትስስር የስራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሀመድ መርሃ ግብሩን በአገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ማስጀመራቸውን ተከትሎ ክልሎች እንዳሉበት ተጨባጭ ሁኔታ መርሃ ግብሩን በይፋ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኦሮሚያ፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሐረሪ እንዲሁም የሲዳማ ክልሎች መርሃ ግብሩን በይፋ ካስተዋወቁት መካከል ሲሆን ሌሎች ክልሎችም በቅርቡ በይፋ ስራዎች ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በመገኘት መርሃ ግብሩን በይፋ ባስተዋወቀቁበት ወቅት የሌማት ትሩፋት የትውልድ ግንባታ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንድናውል ያግዘናል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል የሌማት ትሩፋት ማስተዋወቂያ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክን በሀላባ ቁሊቶ ከተማ አካሂዷል፡፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደረጃ መርሃ-ግብሩ ይፋ ሲደረግም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው፤ መርሃ-ግብሩ ክልሉ ለእንስሳት እንዲሁም ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ያለውን ዕምቅ ሀብት ለመጠቀም እንደሚያግዝ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በወተት፣ ስጋ፣ ዶሮና እንቁላል ላይ በማተኮር ሁሉንም አርሶ እና አርብቶ አደር በማሳተፍ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በተመሳሳይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ኦርዲን በድሪና የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደስታ ሊዳሞ፤ መርሃ-ግብሩ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ስርዓተ ምግብን ከማሻሻል ባሻገር ለኢትዮጵያ መጻኢ የብልጽግና ጉዞ መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በውጤታማነት ገቢራዊ እንዲሆን ከሚሰሩ ባለድርሻ ተቋማት ማካከል ደግሞ በዘርፉ ያሉ የምርምር ተቋማት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የምርምር ማዕከላት በተለይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በተለይ የተሻሻሉ ዶሮዎችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ግቡን እንዲመታ የተሻሻሉ የዶሮ እና የእንስሳት ዝርያዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ የዶሮ ተመራማሪና የብሔራዊ ዶሮ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ሚስባህ ሀላዊ፤ የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ደረጃ 220 እንቁላል እንዲሁም በአርሶ እና አርብቶ አደር ደረጃ ደግሞ በዓመት እስከ 150 እንቁላል መስጠት የሚችሉ "ኮኮክ" የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን በማላመድ ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ማሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

በምርምር ደረጃ 240 እንዲሁም በአርሶ አደር ደረጃ ደግሞ በዓመት እስከ 200 እንቁላል መስጠት የሚችሉ "ዲ ዜድ ዋይ" የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን ለማሰራጨት ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ፤ የስጋና ወተት እንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል የውጭ ሀገራት ዝርያያላቸው ኮርማዎችን በማዳቀል ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮችም በመርሃ ግብሩ ያላቸውን ተስፋ ከወዲሁ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ በደቡብ ክልል ጊዲቦ ቀበሌ ካነጋገራቸው አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ትክክል ቦጋለ መርሃ-ግብሩ በተለይ የገቢ ምንጫቸውን ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተስፋ ሰንቀዋል፡፡

ለዚህም አንድ ሺህ ጫጩቶችን ገዝተው ለማርባት ክፍያ መፈጸማቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

ለመርሃ ግብሩ እውን መሆን ደግሞ በተለይ አመራሩ ኀብረተሰቡን በማስተባበር በቁርጠኝነት የመስራት ኃላፊነት አለበት፡፡

መርሃ-ግብሩ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ነጻ አገር እውን ማድረግን ያለመ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ፤ አመራሩ ይህንን ተገንዝቦ እንዲሰራ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ህልም የሚመስሉ በርካታ አገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ የቻለችው በዜጎቿ የተባበረ ክንድ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በምግብ ራስን ከመቻል በላይ የኢትዮጵያን የአምራችነት ታሪክ የመቀየር ግብ ለሰነቀው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መስራት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም