የኢትዮጵያንና የሶማሊያን የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ ደረጃ ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ተካሄደ

155

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላህ አህመድ ጃማ ጋር የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ ደረጃ ማጠናከር የሚያስችል ምክክር አካሂደዋል።

ሁሉቱ መሪዎች በኒጀር ኒያሚ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባዔ ጎን ለጎን ባካሄዱት ምክክር የኢትዮጵያንና የሶማሊያን የባለብዙ ወገን ትስስርና አጋርነት በማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በላቀ ሁኔታ ለማሳደግ ተስማምተዋል።

ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ መላቅ አስተዋጽኦ የሚኖረውን የጋራ የሚኒስትሮች ጉባኤም በአፋጣኝ ለማካሄድ መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ለሶማሊያ ለማካፈል ዝግጁ ናት።

የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላህ አህመድ ጃማ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ለሶማሊያም ሆነ ለቀጠናው ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ በቀጠናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር ናት ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም