በዓሉን ስናከብር የልማት ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ በመነሳሳት ሊሆን ይገባል

81

አሶሳ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን ስናከብር አንድነታችንን በማጠናከር የልማት ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ አሳሰቡ።

"ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሠላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት ምክትል አፈ ጉባኤዋ ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ሆና ወደፊት እየገሰገሰች ነው ብለዋል።  

ይህም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በፈተና በማይነቃነቅ የፀና መሠረት ላይ መሆናቸውን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

የዘንድሮን የብሔሮች፣ ብሔራሰቦችና ህዝቦችን ቀን ስናከብር አንድነታችንን በበለጠ በማጠናከር የልማት ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ  በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።

የክልሉ ህዝቦች ለዘመናት የቆየውን የመቻቻል ባህላቸውን በማጠናከር የሃገራቸውን ልማት ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲተጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።  

በፓናል ውይይቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የህግ  አማካሪ አቶ መሃመድ ሃሚድ የፌደራሊዝም ጽንሰ ሃሳብና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።  

በውይይቱ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም